አቋም/ዶርትሙንድ በመድፈኞቹ በተፈለገው በፕየር ኤምሪክ አውባሚያንግ ዝውውር ዙሪያ ላይ የመጨረሻ አቋሙን አሳወቀ

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በአርሰናል በጥብቅ በሚፈለገው በጋቦናዊው አጥቂ ፕየር ኤምሪክ አውቦሚያንግ የዝውውር ዙሪያ ግልፅ አቋሙን አሳወቀ።

<!–more–>

ትናንት ምሽት በሲግናል ኢዱናል ፓርክ ፍራይበርግን አስተናግዶ 92ኛ ደቂቃ ላይ የአቻነቷን ጎል በማስቆጠር ከሽንፈት የተረፉት ዶርትሙንዶች ከዝውውር ጋር  ስሙ የተያያዘው ኦውባሚያንግን በቋሚ አሰላለፍ ላይ በማስገባት ተጠቅመዋል።

ተጫዋቹ ከስነ ምግባር ጋር ተያይዞ ባለፈው ሳምንት ከቡድኑ ውጪ የነበረ በመሆኑ ወደ አርሰናል የሚያደርገው ዝውውር ለማጠናቀቅ ጥሩ አጋጣሚ የተፈጠረለት መስሎ ነበር።

አሌክሲስ ሳንቼዝ፣ዋልኮት እና ኮክለንን ያጡት መድፈኞቹ የዝውውሩ ቀነ ገደቡ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ምናልባትም ኢሊቬ ዥሩን አሳልፈው ለሌላ ቡድን ሊሰጡ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል።

ነገርግን ዥሩ ከክለቡ ከመልቀቁ በፊት አርሰናሎች የኦባሚያንግን ዝውውር በቅድሚያ ማጠናቀቅ እንደሚፈልጉ ታውቋል።

ዶርትሙንድ ጋቦናዊ አጥቂውን ለመሸጥ ፍላጎት ያሳየ ቢሆንም ለዝውውሩ ያስቀመጡት ሂሳብ አርሰናሎች ካቀረቡት ጋር ሊጣጣም አልቻለም።

መድፈኞቹ ሁለት ጊዜ የተሻሻለ ሂሳብ ቢያቀርቡም ተቀባይነትን ግን አላገኘም።በሁለቱ ክለቦች መካከልም እስከ 10 ሚሊየን ፓውንድ የሚሆን ልዩነት መፈጠሩን ነው የተለያዩ መረጃዎች እየጠቆሙ የሚገኙት።

አሁን ደግሞ የተጫዋቹ ክለብ በስፖርት ዳይሬክተሩ ሚሼል ዞርክ አማካኝነት በዝውውሩ ዙሪያ ላይ የመጨረሻ አቋሙን አሳውቋል።

“ዝውውሩን ባስቀመጥነው ልክ ለማከናወን ተዘጋጅተናል።ነገርግን ይህን ለማድረግ የጠየቅነው መሟላት አለበት።

“አርሰናል እስካሁን ድረስ ብዙ ሙከራዎችን አድርጓል፣ነገርግን ሁሉን ጥያቄዎቻቸውን እኛ ውድቅ አድርገንባቸዋል።

“እነሱ እኛ የጠየቅነውን የሚያሟሉ ከሆነ ተጫዋቹን እንለቀዋለን ያ የማይሆን ከሆነ ግን ተጫዋቹ እስከ ክረምት ድረስ ከኛ ጋር ይቆያል።ይህ ደግሞ ከሱ ቤተሰቦች ጋር ጭምር ተወያይተን የተስማማንበት ነገር ነው።” ሲሉ የክለቡን አቋም አሳውቀዋል።

አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ ለዝውውሩ ያቀረበው ሂሳብ 50 ሲሆን ዶርትሙንዶች ደግሞ እስከ 60 ሚሊየን ፓውንድ እንደሚፈልጉ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እሮብ በሚጠናቀቀው የዝውውር መስኮት አርሰን ዌንገር ዶርትሙንዶች የሚፈልጉትን ሂሳብ አቅርበው ተጫዋቹን የግላቸው ያደርጉት ይሆን?

Advertisements