የሩጫ ድግስ / 11ኛው የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ውድድር ተካሄደ

ምስል / ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ይፋዊ ገፅ የተገኘ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ያዘጋጀው 11ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር ዛሬ ረፋድ በሰንደፋ እና ለገጣፎ ከተሞች ተካሂዷል። 

በወንዶች ዘርፍ በተደረገው ውድድር ጌታነህ ሞላ ከመከላከያ በቀዳሚነት ሲፈፅም የሲዳማ ቡናው በተስፋ ጌታሁን እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪኩ ዳዊት ፍቃዱ ውድድሩን በሁለተኛ እና ሶስተኛነት አጠናቀዋል። 

በሌላ በኩል በሴቶች ዘርፍ በተደረገው ውድድር ዘይነባ ይመር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንደኝነት ውድድሯን ስትፈፅም መሰረት በለጠ ከኦሮሚያ ክልል እና በቀለች ጉደታ በግል በሁለተኛ እና ሶስተኛነት ተከታትለው ገብተዋል።

ከፌደሬሽኑ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው ከሆነ በውድድሩም ሶስት ክልሎች፣ አንድ ከተማ አስተዳደር፣ ሃያ ስድስት ክለቦችና ተቋማት፣ እንዲሁም በግል የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች የተካፈሉ ሲሆን 147 ሴትና 414 ወንድ አትሌቶች በድምሩ 561 የሚሆኑ አትሌቶች ተሳትፈውበታል።

በውድድሩ ላይ በሁለቱም ፆታ ከ 1ኛ – 3ኛ ለወጡ ሯጮች የሜዳሊያ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ከ 1ኛ – 6ኛ ለወጡ ሯጮች ደግሞ ከ 20,000 ጀምሮ እስከ 3,000 ብር ድረስ ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ተሸልመዋል፡፡

ውድድሩ በመጀመሪያ በመዲናችን አዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ ሊደረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በሚል ምክንያት በሰንዳፋ እና ለገጣፎ ከተሞች እንዲካሄድ ተደርጓል።

            የውድድሩ ዝርዝር የውጤት መግለጫ

በግል ወንዶች

1ኛ. ጌታነህ ሞላ፣ መከላከያ፣ 1፡01፡25 

2ኛ. በተስፋ ጌታሁን፣ ሲዳማ ቡና፣ 1፡01፡33 

3ኛ. ዳዊት ፍቃዱ፣ ኤሌክትሪክ፣ 1፡01፡44 

4ኛ. ጂግሳ ቶለሳ፣ ኦሮሚያ ክልል፣ 1፡02፡13 

5ኛ. አይቶልኝ ካሳው፣ አማራ ማረሚያ፣ 1፡02፡17 

6ኛ. አሰፋ ተፈራ፣ ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ፣ 1፡02፡39

በግል ሴቶች 

1ኛ. ዘይነባ ይመር፣ ባንክ፣ 1፡10፡24 ሰዓት

2ኛ . መሰረት በለጠ፣ ኦሮሚያ ክልል፣ 1፡10፡35 

3ኛ. በቀለች ጉደታ፣ በግል፣ 1፡11፡19 

4ኛ. ዝናሽ መኮንን፣ ኦሮሚያ ፖሊስ፣ 1፡11፡27 

5ኛ. የሺ ካልአዩ፣ መሰቦ 1፡11፡32 

6ኛ. እታፈራሁ ወዳጆ፣ በግል፣ 1፡11፡39

በቡድን ወንዶች

1. መከላከያ፣ በ45 ነጥብ፣ የዋንጫ ተሸላሚ፣

2. ኦሮሚያ ክልል፣ በ54 ነጥብ፣ ሁለተኛ ደረጃ

3. ፌዴራል ፖሊስ፣ በ95 ነጥብ፣ ሶስተኛ ደረጃ

በቡድን ሴቶች

1. ኦሮሚያ ክልል፣ በ44 ነጥብ፣ የዋንጫ ተሸላሚ

2. ባንክ፣ በ46 ነጥብ፣ ሁለተኛ ደረጃ

3. ኦሮሚያ ፖሊስ፣ በ58 ነጥብ፣ ሶስተኛ ደረጃ

Advertisements