ተስፋ / አርሰናል በክለቡ የክብረ ወሰን ዋጋ ኦቦምያንግን ለማስፈረም መቃረቡ ተገለፀ

አርሰናል የክለቡ ክብረወሰን በሆነ 60 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ፒዬር ኤምሪክ ኦቦምያንግን ለማስፈረም መቃረቡ ተገለፀ።  

የሰሜን ለንደኑ ክለብ በጋቦኒያዊው ተጫዋች ዝውውር ዙሪያ ከዚህ ቀደም ያቀረበው ሁለት የዝውውር ዋጋ ተቀባይነት ሳያገኝ ቢቀርም በመጨረሻ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ጋር መስማማቱ ታውቋል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘም የ 28 አመቱን ተጫዋች ዝውውር ለማጠናቀቅ እንቅፋት ሆኖ ያለው ብቸኛ ነገር የጀርመኑ ክለብ የፊት መስመር ኮከቡን ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ምትክ የሚሆነውን ተጫዋች የማግኘቱ ነገር ነው። 

ዶርትሙንድ ለኦቦምያንግ ምትክ የሚሆነውን እስኪያገኝ ድረስም ዝውውሩ እስከ መጪው ረቡዕ ድረስ ሊንጓተት እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን የጀርመኑ ክለብም ኦሊቬ ዢሩን በውሰት ለመውሰድ ጥያቄ ማቅረቡ ተያይዞ ተነግሯል።

ኦቦምያንግ የጀርመኑን ክለብ ለመልቀቅ ለወራት ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በፊትም ከጨዋታ በፊት የነበረን የቡድኑን የውይይት መድረክ ሳይሳተፍ በመቅረቱ እገዳ ተጥሎበት እንደነበር አይረሳም።  

ከሰሞኑ ግን ወደቡድኑ እንዲመለስ ተደርጎ ባሳለፍነው ቅዳሜ ቡድኑ ከፍሬይቡርግ ጋር ባደረገው ጨዋታ የተሰለፈ ሲሆን የቅዳሜው ጨዋታም ከታህሳስ መጀመሪያ በኋላ ሙሉ 90 ደቂቃ መሰለፍ የቻለበት የመጀመሪያ ጨዋታውም ሆኗል። 

አርሰናል ኦቦምያንግን ማስፈረም ከቻለ ባሳለፍነው ክረምት አሌክሳንደር ላካዜቲን በ 52 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ያስፈረመበትን የክለቡን ክብረ ወሰን ዋጋ በስድስት ወራት ልዩነት ውስጥ በድጋሚ የሚሰብር ይሆናል። 

Advertisements