ይፋዊ / ዳንኤል ስተሬጅ ዌስትብሮሚች አልቢዮን ተቀላቀለ

በሊቨርፑል የመጫወት እድል ማግኘት ያልቻለው እንግሊዛዊው ዳንኤል ስተሬጅ ላለመውረድ እየታገለ ለሚገኘው የአለን ፓርዲው ዌስትብሮም ተቀላቅሏል።

ተጫዋቹ ጥሩ አቅም እንዳለው ቀደም ብሎ ማሳየት ቢችልም ተደጋጋሚ ጉዳቶች የጫወታ ጊዜውን እያሳጠሩት መጥተዋል።

ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ ከተመለሰ በኋላም የየርገን ክሎፕ ቡድን ውስጥ ሰብሮ መግባት ባለመቻሉ በቂ የመጫወት እድል ለማግኘት አልቻለም።

ተጫዋቹ የፊታችን ሰኔ ወር ላይ ለሚካሄደው  የ2018 የአለም ዋንጫ ላይም የጋሪዝ ሳውዝጌት ቡድን ውስጥ የመካተት ፍላጎት ቢኖረውም ከሊቨርፑል ጋር ቆይቶ ፍላጎቱን ለማሳካት እንደሚከብደው ተረድቶታል።

በዚህ ምክንያትም በቂ የመጫወት እድል ለማግኘት ወደ ዌስትብሮም በውሰት ውል ማቅናቱ ይፋ ሆኗል።

በጥር የዝውውር መስኮት አንድ አጥቂ ለማስፈረም ፍላጎት የነበራቸው አለን ፓርዲው በኤፍ ኤ ካፑ ሊቨርፑልን ካሸነፉ በኋላ ስለ ዳንኤል ስተሬጅ የቀረበላቸው ጥያቄን ምላሽ ለመስጠት አልፈለጉም።

ስተሬጅን ለማስፈረምም ኒውካስትል፣ሲቪያ እና ኢንተር ሚላን ፍላጎት አሳይተው የነበረ ሲሆን በተለይም ኒውካስትል ፍላጎቱን በግልፅ ለሊቨርፑል በመግለፅ የተጫዋቹ ማረፊያ ለራፋ ቤኒቴዙ ቡድን መስሎ ነበር።

ነገርግን በበርኒግሀም የተወለደው ስተሬጅ ምርጫው ወደ ትውልድ አካባቢው በማድረግ ለዌስትብሮም ፈርሟል።

ተጫዋቹ በአዲሱ ክለቡ በፕሪምየርሊጉ ላይ ሳይወርድ እንዲሰነብት ለማድረግ በቀሪዎቹ የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ጨዋታዎች ወደ ጎል አስቆጣሪነቱ በፍጥነት መመለስ ይጠበቅበታል።

Advertisements