ሁዋን ማታ በቀያይ ሰይጣኖቹ ቤት ያለውን ውል አራዘመ


ስፔናዊው ጥበበኛ አማካይ ሁዋን ማታ በማንችስተር ዩናይትድ ያለውን የቆይታ ውል በአንድ አመት አራዝሟል፡፡

በክለቡ ደጋፊዎች እጅጉን ከሚወደዱ ተጫዋቾች መካከል ዋነኛ የሆነው ማታ የጆዜ ሞሪንሆ ወደኦልትራፎርድ መምጣትን ተከትሎ ቆይታው አጠራጣሪ ነው ሲባል ቢቆይም በአሰልጣኙ ተመራጭ ከመሆኑም በላይ በቀያዮቹ ቤት ለተጨማሪ ጊዜ የሚቆይበት ዕድል ተፈጥሮለታል፡፡

የ8 ቁጥሩን ስፔናዊ ኮከብ ውል ማራዘም አስመልክቶ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ከክለቡ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ “ማታ በጣም ጠቃሚ ተጫዋች ነው ፤ ወደዚህ ስመጣ ‘ማታ ችግር ውስጥ ነው’  ፣ ‘ማታ መባረሩ ነው’ የሚሉ አስተያየቶች በርክተው ነበር፡፡ አሁን ግን ጭራሽ ውሉን አራዝመናል፡፡
ለኔ በጣም ከሚያስፈልጉኝ ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ በተጨማሪም ለክለቡም ሆነ ለሌሎች ተጫዋቾች አስፈላጊ የሆነ ስብህና ያለው ሰው ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ሁዋን ማታ በበኩሉ “እዚህ በመገኘቴ ዕድለኛ ነኝ፡፡ ከአለማችን ታላላቅ ክለቦች ዋነኛው ነው፡፡ በክለቡ ፣ በደጋፊዎቹና በአሰልጣኙ ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡

በጥር 2014 የዝውውር መስኮት በጊዜው የቼልሲ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ አማካኝነት ለማንችስተር ዩናይትድ የተሸጠው ማታ በዩናይትድ ቤት 172 ጨዋታዎችን አድርጎ 39 ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል፡፡

Advertisements