ልዩ ጥንቅር / የዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ምሽት የተሳኩ እና ያልተሳኩ የዝውውር ሂደቶች፣ አስተያየቶች፣ ቁጥሮች እና ሌሎች መረጃዎች

በመጨረሻ የዝውውሩ መጠናቀቂያ ዕለት ከተፈፀሙ ትልልቅ ዝውውሮች ስንጀምር ፒዬር ኤምሪክ ኦቦምያንግ ዶርትሙንድን በመልቀቅ በ 56 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ አርሰናልን ተቀላቅሏል።

በሌላ በኩል የጋቦናዊው ወደኢምሬትስ መምጣት ይበልጥ ቦታውን እንደሚያሳጣው ሳይታለም የተፈታው ኦሊቬ ዢሩ በ 17.5 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ወደ ቼልሲ አምርቷል።

ከዝውውሩ መጠናቀቅ በኋላም “እኔ ትኩረቴ በቋሚነት መጫወት ስለምችልበት ሁኔታ ነው። ለእኔ ወሳኙ ነገር ከአሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ንግግር ማድረጌ ነው። 

“እሱ እንደሚፈልገኝ ተረድቻለሁ። ከእኔ ጋር ለመስራት የእውነትም ፍላጎት አለው።” ሲል ፈረንሳዊው አጥቂ በዝውውሩ ዙሪያ ያለውን ስሜት ገልጿል።

ትኩረታችንን በማውሪሲዮ ፖቸቲኖው ቶትነሀም ላይ ስናደርግ ደግሞ የፒኤስጂውን የክንፍ መስመር ተጫዋች ሉካስ ሞራ መፈረም እናገኛለን። 

የ 25 አመቱ ብራዚላዊ ከሀገሩ ልጅ ኔይማር እና ክልያን ምባፔ ወደ ፒኤስጂ መምጣት ወዲህ በፓሪሱ ክለብ የቋሚ ተሰላፊነት እድል የራቀው መሆኑን ተከትሎ ከእድሜው ጋር አቻ ስሌት ባለው 25 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ የሰሜን ለንደኑን ክለብ በአምስት አመታት ከግማሽ የውል ስምምነት ተቀላቅሏል።

በ 2013 የሀገሩን ክለብ ሳኦፓሎ በመልቀቅ በ 38 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ ወደፒኤስጂ ተቀላቅሎ የነበረው ሞራ በኳታር መንግስት በሚዘወረው የፈረንሳዩ ክለብ 229 ጨዋታዎችን አድርጎ 46 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። 

“ወሳኙ ነገር መሰለፍ መቻል ነው። እንደማስበው ይህ ተሰጥኦዬን እና ብቃቴን የማሳይበት አዲስ ፈተና ያለበት ቦታ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ቶትነሀም ትልቅ ክለብ ነው። የክለቡ ታሪክ በጣም በጣም የሚማርክ ነው።  

“ለቶትነሀም መጫወት ትልቅ ደስታ ነው። አሁን ፍላጎቴ ብዙ ሳልጨነቅ ጠንክሬ መስራት እና ብቃቴን ማሳየት ነው።” በማለትም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ስድስት ጨዋታ ብቻ እሱንም ከተቀያሪ ወንበር ላይ እየተነሳ ያደረገው ሙራ በዝውውሩ ዙሪያ ያለውን ስሜት ገልጿል። 

በሌላ በመጨረሻ ሰዓት የተጠናቀቀ ዝውውር ስቶክ ሲቲ በ 14 ሚሊዮን ፓውንድ የጋላታሳራዩን ሴኔጋላዊ የመሀል ሜዳ ሞተር ባዱ ኒዲያዬን ማስፈረም የቻለ ሲሆን ተጫዋቹንም ከዋትፎርድ ጋር በነበረው የምሽቱ ጨዋታ እረፍት ሰዓት ላይ ለደጋፊዎቹ አስተዋውቋል።  

ክሪስታል ፓላስ በበኩሉ በመጨረሻዎቹ የዝውውር ሰዓታት ኖርዌያዊውን የ 22 አመቱን አጥቂ አሌክሳንደር ሶርሎዝን በ 8.7 ሚሊዮን ፓውንድ የቅድሚያ የዝውውር ሂሳብ በእጁ ማስገባት ችሏል።  

በሌላ መረጃ ደግሞ የሽሩለስት ፓርኩ ክለብ የሊሉን አማካኝ ኢብራሂም አማዱን ለማስፈረም ጥረት ቢያደርግም የፈረንሳዩ ክለብ ለተጫዋቹ ተተኪ የሚሆነውን በማጣቱ ዝውውሩ ሳይሳካለት ቀርቷል። 

በያዝነው የጥር የዝውውር መስኮት በትልቁ ለመሳተፍ ጥረት ያደረገው ስዋንሲ በበኩሉ ከ 18 ወራት በፊት በ 20 ሚሊዮን ፓውንድ ለዌስትሀም የሰጠውን አንድሬ አዩን በ  18 ሚሊዮን ፓውንድ በማምጣት ዳግም ከስብስቡ ጋር ቀላቅሎታል።

በተያያዘ ሌላ መረጃ የዌስትሀሙ ተከላካይ ሬክ ኦክስፎርድ መደሻዎቹን በመልቀቅ የጀርመኑን ክለብ ቦሩሲያ ሞንቹግላድባህ እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ በውሰት ውል ተቀላቅሏል። 

በዚሁ ወደጉዲሰን ፓርክ ስናመራ ሳም አላርዳይስ ከኤቨርተን አይለቅም ያሉለት አዴሞላ ሉክማን በመጨረሻ ሰዓት በውሰት ውል ወደ ሌላኛው የጀርመን ክለብ አርቢ ሊፕዚግ አምርቷል። 

እዛው ኤቨርተን ቤት ስንቆይ የሲቲው ውድ ተከላካይ ኢሊኬም ማንጋላ የኢትሀዱን ክለብ በመልቀቅ በውሰት ውል እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ወደጉዲሰን ፓርክ ያመራ ሲሆን መሀመድ ቤሲክ በበኩሉ ሚድልስብሮን ተቀላቅሏል።  

ኒውካስትል በበኩሉ የሌስተሩን ኢስላም ስሊማኒን እስከ ውድድር ዘመኑ ፍፃሜ በውሰት ውል በእጁ ያስገባ ቢሆንም በጉዳት ምክንያት የቀበሮቹ ኮከብ ለሁለት ሳምንታት ያህል የጥቁርና ነጩን መለያ የማይለብስ ይሆናል። 

እዛው ኒውካስትል ቤት ስንቆይ ሄነሪ ሳቪየት የቱርኩን ሲቫስፑር እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ በውሰት የተቀላቀለ ሲሆን ሮላንዶ አሮንስ በበኩሉ ወደሄላ ቬሮና አቅንቷል። 

ዋትፎርድ በበኩሉ የሰንደርላንዱን አማካኝ ዲዲየር ንዶንግን በውሰት ሲያስፈርም ኮስትል ፓንቲሊሞን በተመሳሳይ የውሰት ውል ወደኖቲንግሀም ፎረስት አሻግሯል።  

በዝውውር መስኮቱ ምንም አይነት የረባ እንቅስቃሴ ያላደረገው የኦልትራፎርዱ ማንችስተር ዩናይትድ የቼኩን የ 18 አመት ግብ ጠባቂ ማቲጅ ኮቫርን ከስሎቫኮ በማስፈረም ታዳጊውን በእጁ አስገብቷል።  

ተስፈኛው ታዳጊ ባሳለፍነው ጥቅምት ወደኦልትራፎርድ በመምጣት የአንድ ሳምንት አስደናቂ ሙከራን ያደረገ ሲሆን ፕሮፌሽናል የውል ስምምነት በመፈራረምም ከዩናይትድ ጋር ያለውን ቆይታ አጠንክሯል። 

ሌስተር በበኩሉ የ 17 አመቱን ታዳጊ የክንፍ መስመር ተስፈኛ ካሉም ራይትን በእጁ ያስገባ ሲሆን አማካኙን አንዲ ኪንግን ደግሞ ወደስዋንሲ በውሰት እንዲቀላቀል ፈቅዶለታል። 

ከዚህ በተጨማሪም ወደሲቲ እንደሚያመራ ሲነገርለት የነበረውን ሪያድ ማህሬዝን በተመለከተ ሌስተር የለጠፈበትን 90 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ የኢትሀዱ ክለብ ለመክፈል ባለመፈለጉ ዝውውር ሳይሳካ ቀርቶ ተጫዋቹ በኪንግ ፓወር እንዲቆይ ሆኗል። 

ጉዞዋችንን ወደ መርሲሳይድ ስናደርግ ደግሞ በየርገን ክሎፕ የሚመራው ሊቨርፑል አራት ተጫዋቾቹን በውሰት ውል ለተለያዩ ክለቦች ሰጥቶ እናገኛለን። 

በዚህም መሰረት ኦቪዬ ጃሪያ ወደ ሰንደርላንድ፣ ጆን ፍላንጋን ወደቦልተን፣ ላዛር ማርኮቪች ወደ አንደርሌክት እና ሀሪ ዊልሰን ወደ ሁል ሲቲ አቅንተዋል።  

የመድፈኞቹ ፈረንሳዊ ተከላካይ ማቲው ደቡቺ በበኩሉ ኢምሬትስን በመልቀቅ የሀገሩን ክለብ ሴንት ኢትዬንን እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ድረስ ተቀላቅሏል። 

የ 32 አመቱ ተጫዋች በአርሰናል የነበረውን አስከፊ ቆይታ ተወት በማድረግ በ 18 አመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን ወዳደረገበት እና የመጀመሪያ ክለቡ ወደሆነው ኢትዬን አምርቷል።

ሌሎች የፕሪምየር ሊጉን የውሰት ስምምነቶች ስንመለከት ደግሞ የቼልሲው ቶድ ኬን ወደ ኦክስፎርድ ሲያመራ የማንችስተር ሲቲው ጃኮብ ዴቨን ፖርት ብራይተን አልቢየንን ተቀላቅሏል። 

ከእንግሊዝ ወጣ ብለን የመላው አውሮፓን የጥር የዝውውር መስኮት በጨረፍታ ስንመለከት በአጠቃላይ ባለፋት 30 ቀናት አምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊግ ክለቦች 518 ዝውውሮችን ሲፈፅሙ 792.7 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ አድርገዋል።

ከ 792.7 ሚሊዮን ፓውንዱ ፕሪምየር ሊጉ 202 ዝውውሮችን በማሳካት እና 545.6 ሚሊዮን ፓውንድ በማፍሰስ በቀዳሚነት ሲቀመጥ ላሊጋው በ 99 ዝውውሮች እና በ 303.5 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ በተከታይነት ተቀምጧል።

ቡንደስሊጋ፣ የፈረንሳይ ሊግ እና የጣሊያን ሴሪ አ ደግሞ ተከታታዮቹን ደረጃዎች ይዘው አጠናቀዋል። የመጪው የክረምት የዝውውር መስኮት እስኪጀመር ድረስም መልካም ቆይታን ተመኝተን የመጨረሻ ዕለት የዝውውር ፍፃሜ ዳሰሳችንን አጠናቀናል።

Advertisements