ጅማሮ / የብርሀንና ሰላም ማተሚያ ደርጅት በሁለት የስፖርት አይነቶች ክለቦችን ለማቋቋም ከጫፍ መድረሱን አበሰረ

የብርሀንና ሰላም ማተሚያ ደርጅት በአትሌቲክስ እና ብስክሌት ዘርፎች ላይ ያተኩሩ ሁለት ክለቦችን ለማቋቋም ከጫፍ መድረሱን በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብስሯል፡፡

ማተሚያ ቤቱ በ 2010 የበጀት አመት ከ 4.5 ሚሊዮን በላይ ብር በመመደብ በተጠቀሱት ሁለት የስፖርት አይነቶች ክለቦችን ለማቋቋም አስፈላጊው ስራዎች ተጠናቀው የአሰልጣኞችና ስፖርተኞችን ቅጥር መጨረሱ ተገልጿል፡፡ 

አዲስ እየተቋቋሙ ያሉት የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች ባደረጉት የስፖርተኞች ምልመላም በአትሌቲክስ ዘርፍ ስድስት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች በድምሩ ስምንት ስፖርተኞች ሲመለመሉ በብስክሌት ዘርፍ አምስት የወንድ የኮርስ ብስክሌት ተወዳዳሪ ስፖርተኞች በአባልነት መያዛቸው ተያይዞ ተገልጿል፡፡

ማተሚያ ቤቱ የቤተሰብ እግር ኳስ ውድድር ማድረግ ከጀመረበት 1956 አንስቶ በጠረጴዛ ቴኒስ፣ በአትሌቲክስ እና መረብ ኳስ ክለብ እስከማቋቋምና የተለያዩ ውድድሮች ላይ በመካፈል የዋንጫ አሸናፊ እስከመሆን የደረሰ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን የበጀት እጥረትን በመሰሉ ችግሮች ከመድረክ ጠፍቶ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ድርጅቱ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) በሚያዘጃቸው ውድድሮች ላይ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በመሳተፍ የዋንጫ እና የሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን በሰራተኞቹ የተመዘገበውን ውጤትም በመደበኛ መልኩ በሚያስቀጥል ሁኔታ ክለብ ለማቋቋም ሂደቱን እያጠናቀቀ ነው፡፡         

በኢትዮጵያ የህትመት ኢንዱስትሪ ጉዞ ላይ ግንባር ቀደም እና አንጋፉ የሆነው ማተሚያ ቤቱ በቀጣይም ከአትሌቲክስና ከብስክሌት በተጨማሪ የእግር ኳስ ክለብ ለማቋቋም እቅድ እንዳለው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተወስቷል፡፡ 

Advertisements