ጆሴ ሞሪንሆ ፌሌይኒ ተቀይሮ ከገባ ከ ሰባት ደቂቃ በኋላ ለምን መልሰው እንደቀየሩት አሳወቁ

ማንችስተር ዩናይትዶች ወደ ለንደን አቅንተው በቶተንሀም ሆትስፐር በተሸነፉበት ምሽት ቤልጄማዊው ማርዋን ፌሌይኒ 63ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ገብቶ 70ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ የተቀየረበትን ምክንያት ጆሴ ሞሪንሆ ከጨዋታው በኋላ አስረድተዋል።

ቀያይ ሰይጣኖቹ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር በቶተንሀም ተሸንፈው ለንደንን አንገታቸውን አቀርቅረው ለመልቀቅ ተገደዋል።

በተከላካይ ቦታ ላይ የጆሴ ሞሪንሆ ቡድን መሆኑን እስኪያጠራጥር ድረስ ያልተረጋጋ እና ያልተደራጀ የነበረው ዩናይትድ የሰሯቸው ሁለት ስህተቶች ለሽንፈት አብቅቷቸዋል።

ክርስቲያን ኤሪክሰን በ11ኛው ሰከንድ ላይ ያስቆጠራት ፈጣኗ ጎል ቡድኑን በጥሩ ስነ ልቦና ጨዋታውን እንዲጀምሩ ስታደርግ ዩናይትዶችን ያስደነገጠች ነበረች።

የሚገርመው ጨዋታው ገና ከመሀል ሜዳ ሲጀምር አብዛኛዎቹ የዩናይትድ ተጫዋቾች ከትኩረት ውጪ ሆነው ኳሱ ወደ ጎል ስትቀየር ከመመልከት ውጪ ብዙም ጥረት አላደረጉም።

ሁለተኛ ጎልም እንዲሁ ከቡድኑ ጋር ረጅም አመት ቆይቶ አሁንም መሻሻል ያልቻለው ፊል ጆንስ በአስገራሚ ሁኔታ በራሱ ጎል ላይ ያስቆጠረው ነበር።

ጆሴ ሁለተኛው ጎል እንደገደላቸው እና ቶተንሀሞች ሊጫወቱ በፈለጉበት መንገድ እንዲጫወቱ እንደረዳቸው ገልፀዋል።

የጨዋታው አስገራሚ ነገር የተፈጠረው ከ 63ኛው ደቂቃ በኋላ ሲሆን በዚህ ደቂቃ ላይ ጆሴ ፌሌይኒን ቀይረው ወደ ሜዳ አስገብተውታል።

የባለሜዳዎቹን የበላይነት ለመግታት ወደ ሜዳ የገባው ፌሌይኒ የታሰበውን ያህል አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ የስፐርሶች የበላይነት በርትቶ ታይቷል።

በአንድ የጨዋታ አጋጣሚም 69ኛው ደቂቃ ላይ ጆሴ ኳስ በሚገባ መቆጣጠር ባልቻለው ቡድናቸው ላይ የብስጭት ምልክቶችን በማሳየት እና እጃቸውን በማወናጨፍ ሄሬራ በፍጥነት ተቀይሮ እንዲገባ ይጠሩታል።

70ኛ ደቂቃ ላይ ሜዳውን እንዲለቅ የተደረገው ግን ሰባት ደቁቃ ብቻ የተጫወተው ማርዋን ፌሌይኒ ነበር።

ተጫዋቹ ሜዳውን ለቆ በቀጥታ ወደ መልበሻ ቤት ያቀናበት ሁኔታ ጆሴ በግዳጅ ሜዳውን እንዲለቅ እንዳደረጉት ምልክት የሚሰጡ ነበሩ።

በዚህ ምክንያት ብዙዎቹ ጆሴ ፌሌይኒን እንዳዋረዱት ቢገልፁም ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኙ የተናገሩት ግን ከዚህ የተለየ ነበር።

“በፌሌይኒ እድለኛ እንዳልነበርኩ አስባለው ምክንያቱም ቀይሬ ያስገባሁት የቡድኑን አደረጃጀት እና እንቅስቃሴ ለመቀየር ነበር ነገርግን ከደቂቃዎች በኋላ ተጫዋቹ ተጎዳ

“እንደ ሁልጊዜው ተመሳሳይ ነገር ነው።ትልቅ ነገር አይደለም፣ቢሆንም ጨዋታውን መቀጠል እንደማይችል ነግሮናል።” በማለት ፌሌይኒ የተቀየረው በጉዳት መሆኑን አሳውቀዋል።

ተጫዋቹ በክረምቱ ኮንትራቱ የሚጠናቀቅ በመሆኑ በጉዳት ጭምር ቡድኑን እያገለገለ ባለመሆኑ በቀጣዩ የዝውውር መስኮት ወደ ሌላ ክለብ የመልቀቁ ነገር እንደማይቀር እየተነገረ ይገኛል።

Advertisements