አፍሪካዊ ተጫዋቾች ላይ በዝውውር ላይ የዘርኝነት አስተያየት የሰጡት የዌስትሀም የምልመላ ዳይሬክተር ከክለቡ ተሰናበቱ

ዌስትሀም ዩናይትድ የክለቡ የተጫዋቾች የምልመላ ዳይሬክተር የሆኑት ቶኒ ሄነሪ በአፍሪካዊያን ተጫዋቾች ላይ በሰጡት ያልተገባ አስተያየት ክለቡ ከሀላፊነታቸው ማባረሩን አሳውቋል።

በእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ የአፍሪካ ተጫዋቾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

የወቅቱ ድንቅ ተጫዋቾች ከሆኑት ውስጥ አፍሪካዊያኖቹ መሀመድ ሳላህ እና ሳዲዮ ማኔ የመሳሳሉት ተጫዋቾች የሚገኙት በዚሁ ሊግ ውስጥ ነው።

በሊጉ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ትላልቅ ቡድኖች እንኳን ቢያንስ አንድ የአፍሪካ ተጫዋቾች በክለባቸው ውስጥ እንዳላቸው መመልከት ይቻላል።

በጥር የዝውውር መስኮት አርሰናል የአጥቂ ክፍሉን ለማጠናከር በክለቡ የዝውውር ሪከርድ ማዘዋወር የቻለው ጋቦናዊውን ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግ መሆኑ ይታወሳል።

በፕሪምየርሊጉ በብዛት የአፍሪካ ተጫዋቾችን ከሚጠቀሙ ውስጥ ደግሞ የለንደኑ ዌስትሀም ዩናይትድ ይጠቀሳል።ክለቡ ላለፉት ረጅም አመታት በርካታ የአፍሪካ ተጫዋቾችን በመጠቀም ይታወቃል።

በተዘጋው የጥር የዝውውር መስኮትም ሁለት አፍሪካዊ ተጫዋቾችን ለማዘዋወር ጥረት ማድረጉ የሚታወስ ቢሆንም የክለቡ የተጫዋቾች የምልመላ ዳይሬክተር የሆኑት ቶኒ ሄነሪ ግን በአፍሪካ ተጫዋቾች ላይ የሰጡት አስተያየት ጦሱ ከክለቡ እንዲሰናበቱ አድርጓቸዋል።

ሰውየው በአስተያየታቸው የአፍሪካ ተጫዋቾች መጥፎ ባህሪ ያላቸው እና በጥባጮች ናቸው በማለት ለወኪሎች ክለቡ አፍሪካዊያንን ማስፈረም እንደማይፈልግ ተናግረው ነበር።

ይህም አስተያየታቸው የቀለም ልዩነት በመፍጠር የተናገሩት በመሆኑ ከክለቡ እንዲሰናበቱ ተደርገዋል።

ዌስትሀም በመግለጫው “ክለቡ ምንም አይነት የዘረኝነት ልዩነቶችን አይታገስም።የክለቡ አባላት ቀለም፣ፆታ፣እድሜ እና ሀይማኖትን ሳይለይ አንድ ህብረት ነው።” በማለት ቶኒ ሄነሪን ማሰናበቱ አሳውቋል።

የክለቡ አሰልጣኝ የሆኑት ዴቪድ ሞይስም አርብ በነበራቸው መግለጫ ላይ ክለቡ ክፍት የሆነ የዝውውር ፖሊስ እንዳለው በመግለፅ ቶኒ ሄነሪ በአፍሪካ ተጫዋቾች ላይ የሰጡት አስተያየት የተሳሳተ መሆኑን አስረድተዋል።

Advertisements