ኢላማ / የርገን ክሎፕ የቀሪውን የውድድር ዘመን የቡድናቸውን እቅድ ይፋ አደረጉ


የርገን ክሎፕ ቡድናቸው የውድድር ዘመኑን አራት ውስጥ ሆኖ ማጠናቀቅ ከቻለ ስኬት መሆኑን ገልፀው ነገርግን እቅዳቸው ከፕሪምየር ሊጉ ክለቦች በልጦ መገኘት እና የሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንደሆነ ተናግረዋል። 

የመርሲሳይዱ ክለብ በኤፍኤ ዋንጫ በዌስትብሮም ከተረታ በኋላ የውድድር ዘመኑ ቀሪ ነገር የቻምፒዮንስ ሊግን ቦታ አግኝቶ ማጠናቀቅ ሲሆን በክሎፕ ስብስብ ውስጥም ቀጣይ የስኬት ኢላማ በአውሮፓ መድረክ ፉክክር ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ መቅረብ መቻል ነው።

ጀርመናዊው አለቃ በሳምንታዊው ጋዜጣዊ መግለጫቸውም ማንችስተር ሲቲ ያሳየውን አስደናቂ አቋም በማውሳት ከዚህ በኋላ የክለባቸው እቅድ የቻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለማግኘት ከመፋለም እንደማይዘል ያመኑበትን አስተያየት ሰጥተዋል።

ክሎፕ ሲናገሩም “የውድድር ዘመንህን ስትጀምር የሆነ ነገር ታልማለህ። ከዚህ በተጓዳኝም ሊሳካ ይችላል የምትለውን ነገር ታልማለህ። እንደማስበው ሻምፒዮን የመሆን እድላችን ህልም ነው። ምክንያቱም ሲቲ ሊጉን ከባድ አድርጎብናል። 

“አንደኛ መሆን ካልቻልክ እኔ ሁለተኛ መሆንን እመርጣለሁ። ነገርግን የውድድር ዘመኑን በሁለተኛነት፣ ሶስተኛነት ወይም አራተኛነት ካጠናቀቅን ሶስቱም ደረጃዎች ለእኔ ጥሩ ናቸው።” በማለት የውድድር ዘመናቸውን ኢላማ ይፋ አድርገዋል።

Advertisements