ስኬት / ሀሪ ኬን ከ 100ኛ የፕሪምየር ሊግ ጎሉ በኋላ ቀጣይ እቅዱን ይፋ አደረገ

ሀሪ ኬን 100ኛ የፕሪምየር ሊግ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ቀጣይ ፍላጎቱ 200 የፕሪምየር ሊግ ግቦች ላይ መድረስ መሆኑን ተናግሮ እዛ ለመድረስም የ 100 ግቦቹን ያህል ጊዜ እንደማይፈጅበት ያለውን እምነት ገልጿል።

የስፐርሱ የፊት መስመር ኮከብ ትናንት ምሽት ቡድኑ በአስደናቂ ሁኔታ ከሊቨርፑል ጋር 2-2 በሆነ አቻ ውጤት በፈፀመው ጨዋታ ላይ በ 95ኛው ደቂቃ የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ሲችል ጎሉም በፕሪምየር ሊጉ ላይ በፈጣን ሁኔታ 100ኛ ግቡን ያስቆጠረ ሁለተኛ ተጫዋች አድርጎታል።

አለን ሺረር በ 124 ጨዋታዎች 100 ግቦችን አስቆጥሮ በቀዳሚነት ሲቀመጥ ኬን 100 ግቦችን ለማስቆጠር 141 ጨዋታዎችን ወስዶበት ተመሳሳይ 100 ግቦችን ለማስቆጠር 147 ጨዋታ ካስፈለገው ሰርጂዮ አግዌሮ ከፍ ብሎ በሁለተኛነት መቀመጥ ችሏል።

በስታዲየሙ ከነበረው ደጋፊ ትልቅ አድናቆትን ያገኘውና ከቡድን አጋሮቹ ደግሞ በልዩ ትዕዛዝ የተሰሩ ጥንድ ጫማዎች የተበረከተለት ኬን ወዲያው ትኩረቱን ለልጅነት ክለቡ 200 የሊግ ግቦችን በፈጣን ሁኔታ ማስቆጠር ላይ አድርጓል።

ኬን ሲናገርም “200 ግቦችን ማስቆጠር አላማዬ መሆን ሲገባ 100 ግብ ለማስቆጠር ከወሰደብኝ ጊዜም በፍጥነት እንደሚሳካ ተስፋ አለኝ። በጊዜ ሂደት እየተሻሻልኩ እንደምሄድም ተስፋ አለኝ። 

“24 አመቴ ነው። ልጅ አይደለሁም፤ ነገርግን ብዙም ትልቅ እድሜ የሚባል አይደለም። ስለዚህም ብዙ የምማራቸው ነገሮች ይኖራሉ። ከአመት አመት ይበልጥ ባለልምድ እና በአካል ብቃት ረገድ ጠንካራ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ያም እንደሚቀጥል ተስፋ አለኝ።” ብሏል።

ኒውካስትል ዩናይትድ ለአለን ሺረርን ስኬት እውቅና ለመስጠት በማሰብ ከሴንት ጀምስ ፓርክ መውጫ ላይ ሀውልት ያቆመለት መሆኑን ተከትሎ በቶትነሀም ተመሳሳይ ነገር ይኖር እንደሆነ የተጠየቀው እንግሊዛዊው አጥቂ ከእራሱ ይልቅ የቡድኑ ስኬት እንደሚያስጨንቀው በመግለፅ ሁኔታውን አስቦበት እንደማያቅ ተናግሯል።

“ስለሀውልት አላስብም። እኔ የማስበው ለቡድኑ ጥሩ የሚሆነውን ነገር ብቻ ነው። ነገርግን  ከመጀመሪያ ጀምሮ ትልቅ ተጫዋች የሚያሰኘውን ነገር አውቄዋለሁ። ጥሩ የሚባል ተጫዋችን ከታላቅ ተጫዋች የሚለየው ነገር ያ ነው። 

“በተከታታይ አመት ብቃትህን ጠብቀህ መቆየት ችለሀል? ሰዎች ሳይጠብቁህ በሂደት እየተሻሻልክ መሄድ ችለሀል? የሚለው ነው ጥያቄው። እኔም እየተገበርኩ ያለሁት እና ወደፊትም ማድረግ የምቀጥለው እሱን ነው። ያ መቼም የማልተወው አስተሳሰቤ እሱ ነው።” በማለትም አቋሙን ገልጿል።

በምሽቱ ጨዋታ የሊቨርፑሉ ተከላካይ ቨርጂል ቫን ዲይክ የ 24 አመቱ አጥቂ ካገኘው አወዛጋቢ ፍፁም ቅጣት ምቶች የመጀመሪያው አውቆ ወድቆ ዳኛውን በማሳሳት ያገኘው እንደሆነ በመግለፅ ትችት ማቅረቡን በተመለከተም የቀዮቹ በረኛ ሎሪስ ካሪየስ ጥፋት እንደፈፀመበት በመናገር ኬን እራሱን ለመከላከል ጥረት አድርጓል። 

Advertisements