ሮናልድ ኪዩመን የሆላንድ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

የቀድሞው የኤቨርተን አሰልጣኝ ሮናልድ ኪዩመን ሆላንድን ወደአለም ዋንጫ የመመለስ አላማን በማንገብ የብርትኳናማዎቹ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል፡፡

አሰልጣኙ እስከ 2022 ድረስ የሃገሪቱ አሰልጣኝ ሆነው ለመስራት ፊርማቸውን ያኖሩ ሲሆን ፈጣን ተፅዕኖን በቡድኑ ላይ ከማሳረፍ ባለፈ ብሔራዊ ቡድኑን ለኳታሩ የ2022 የዓለም ዋንጫ ማድረስ ዋነኛ ኃላፊነታቸው እንደሆነ በፊርማ ስርአቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ባለፈው ጥቅምት ወር ከኤቨርተን የአሰልጣኝነት ስራቸው የተሰናበቱት ኪዩማን ከስንብታቸው በኋላ ያለስራ ተቀምጠው የሰነበቱ አሁን በህይወት ዘመናቸው 10ኛ የሆነውን የዋና አሰልጣኝነት ስራ ሃገራቸውን በመምራት ጀምረዋል፡፡

በተጫዋችነት ዘመናቸው በሆላንድና በባርሴሎና መለያ የማይረሱ ታሪኮችን መፃፍ የቻሉት የ54 አመቱ ኪዩመን የዋና አሰልጣኝነት ስራቸውን በቪትስ አርንሄም የጀመሩ ሲሆን ከዛ በኋላም በአያክስ ፣ በቤኒፊካ ፣ በፒኤስቪ ሄንደሆቨን ፣ቫሌንሺያ ፣ኤ ዚ አልክማር ፣ ፌይኖርድ ፣ ሳውዛምፕተንና ኤቨርተን ማሰልጠን መቻሉ ይታወሳል፡፡
የሆላንድ ብሔራዊ ቡድን በመጪው ክረምት ለሚካሄደው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያውን ማለፍ ተስኖት ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ይታወቃል፡፡

Advertisements