የተረጋገጠ / ፓትሪስ ኤቭራ ዌስትሀም ዩናይትድን ተቀላቀለ

የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ግራ ተመላላሽ ፓትሪስ ኤቭራ በነፃ ዝውውር ዌስትሀም ዩናይትድን ተቀላቅሏል። 

የ 36 አመቱ ተጫዋች በዛሬው ዕለት ጠዋት በረሽ ግሪን የልምምድ ስፍራ በመገኘት የህክምና ምርመራ አድርጎ እስከ ሰኔ 2018 ከመዶሻዎቹ ጋር የሚያቆየውን የአጭር ጊዜ የውል ስምምነት ተፈራርሟል።

የዜናው ምንጭ ስካይ ስፖርት እንደፃፈው በቀድሞው የጁቬንቱስ፣ ሞናኮ እና ማርሴይ ተከላካይ ዙሪያ ኤቨርተንም ፍላጎት አሳድሮ የነበረ ሲሆን ኤቭራ ግን ወደጉዲሰን ፓርክ ከማምራት ይልቅ የለንደኑን ክለብ ምርጫው አድርጎ ለዌስትሀም ፊርማውን አኑሯል።

ኤቭራ ከዝውውሩ መጠናቀቅ በኋላ ከአዲስ ክለቡ ይፋዊ ድረገፅ ጋር በነበረው ቆይታ “መዶሻ በመሆኔ እና ዳግም ወደምወደው ፕሪምየር ሊግ በመመለሴ በጣም ተደስቻለሁ። መመለሴ በጣም አስደናቂና ዌስትሀምም ይህን እድል ስለሰጠኝ ምስጋና የሚገባው ነው። 

“ከእንቅልፌ ስነሳ ጠንክሬ የምሰራበት እንዲሁም ከቡድን አጋሮቼ ጋር አብሬ የማሳልፈው ጊዜ መኖሩን በማወቄ ዌስትሀምን፣ ሊቀመንበሩን፣ አመራሮቹን፣ አሪፍ አቀባበል ያደረጉልኝን አዲሶቹን የቡድን አጋሮቼን እና ወንድሜና ወኪሌን ላመሰግን እፈልጋለሁ።” ሲል ስሜቱን ገልጿል። 

ስምንት አመታትን በኦልትራፎርድ ያሳለፈው ኤቭራ ከወራት በፊት በኢሮፓ ሊግ ግጥሚያ ደጋፊ በመማታቱ የተነሳ ከአውሮፓ መድረክ ውድድሮች የዘጠኝ ወራት ቅጣት የተላለፈበት መሆኑን ተከትሎ ከቀድሞ ክለቡ ማርሴይ ተለያይቶ ያለክለብ ቆይቷል።

ፈረንሳዊው ተከላካይ በአዲሱ ክለቡ 27 ቁጥር መለያ የተሰጠው ሲሆን ዌስትሀም በሜዳው ዋትፎርድን በሚያስተናግድበት ፍልሚያ የመጀመሪያ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

Advertisements