ጉብኝት / ታሪካዊው የፊፋ አለም ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ ወደኢትዮጵያ ሊመጣ ነው

ታሪካዊው የፊፋ አለም ዋንጫ በአለም የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ እና የለስላሳ መጠጥ ኢንዱስትሪ ኮካኮላ ትብብር በመላው አለም እያደረገ ካለው ጉብኝት ጋር በተያያዘ በመጪው የካቲት 17 ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ ነው። 

በትናንትናው ዕለት ቀትር ረቡዕ በሂልተን ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለአራተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ታሪካዊው ዋንጫ ጉዞ ከመጪው የሩሲያ አለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ የአለም እግር ኳስ አፍቃሪያን የውድድሩን ስሜት ከወዲሁ እንዲያጣጥሙ ለማድረግ የታቀደ ነው። 

በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ የኮካ ኮላ ብራንድ ማናጀር የሆኑት ወ/ት ትዕግስት ጌቱ የዋንጫውን ወደኢትዮጵያ መምጣት በማስመልከት ባደረጉት ንግግር “ይህንን የፊፋ አለም ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ማምጣት በመቻላችን ትልቅ ኩራት ይሰማናል። 

“ይህን እድል የኢትዮጵያ ህዝብ ለእግር ኳስ ስፖርት ላለው የማይሞት ፍቅር የተሰጠውን እውቅናና ክብር የሚያሳይ ነው። ዋንጫው በአፍሪካ ውስጥ 10 ሀገራትን የሚጎበኝ ሲሆን ኢትዮጵያ ከነዚህ ሀገራት ውስጥ አንዷ መሆኗ ኮካኮላ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ትልቅ ክብር ያሳያል። 

“እግር ኳስ በአለም ዙሪያ እጅግ ተወዳጅ እና ተፈቃሪ ስፖርት ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአለም ህዝቦች በሀገራቸው እና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ይከታተላሉ። የፊፋ አለም ዋንጫ ደግሞ በእነዚህ ሀገራት ያሉ ከልጅ እስከ አዋቂ የሚገኙ ህዝቦችን በማስተሳሰር ለሚመርጡት ቡድን ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።

“እግር ኳስ በባህል፣ በሀይማኖት እና ፖለቲካ ሳይገደብ ህዝቦችን አንድ የማድረግ ሀይል አለው። ኮካኮላ ይህንን የፊፋን አለም ዋንጫ የመመልከት የተለየ አጋጣሚ ለኢትዮጵያውያን ለማካፈል በመቻላችን ትልቅ ደስታ ይሰማናል።” ብለዋል። 

ታሪካዊው ዋንጫ የካቲት 17 አዲስ አበባ ኤርፖርት ሲደርስ የሀገሪቱ ባለስልጣናት እና የለስላሳ መጠጥ አምራቹ ድርጅት የኢትዮጵያ ሀላፊዎች በተገኙበት የደመቀ አቀባበል ተደርጎለት በብሔራዊ ቤተመንግስት ወደሚደረገው ስነስርዓት ያመራል።

በመቀጠልም ታሪካዊው ዋንጫ ለጋዜጣዊ መግለጫ ወደ ሂልተን ሆቴል አምርቶ ከመግለጫው መጠናቀቅ በኋላ ከዋንጫው ጋር የፎቶ መነሳት ስነስርዓት ተካሂዶ የዋንጫው የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ቀን ውሎ ይቋጫል።

የሁለተኛ ቀን ውሎው ደግሞ ዋንጫው በሀገሪቱ ከሚገኙ የስፖርት አፍቃሪያን ጋር እንዲያሳልፍ የሚደረግበት እና ከታሪካዊው ዋንጫ ጋር አስደሳችና አዝናኝ ውሎ ተደርጎ በግዮን ሆቴል መርሀ ግብሩ የሚጠናቀቅበት ነው። 

በሩሲያ አስተናጋጅነት ከሚደረገው መጪው አለም ዋንጫ በፊት በ 51 ሀገራት ያሉ 91 ከተሞችን ለማዳረስ እቅድ ተይዞለት ባሳለፍነው መስከረም ከሞስኮ ጉዞውን የጀመረው ታሪካዊው ዋንጫ ዘጠኝ ወራትን በሚፈጅ ረጅም ጉዞው 126 ሺህ ኪ.ሜ ያቆራርጣል። 

የትክክለኛ ዋንጫው ንድፍ በ 1974 የተሰራለት እና 6.142 ኪ.ግ የሚመዝነው የፊፋ አለም ዋንጫ አለም የሚሳሳለት ውድ ሽልማት እንደመሆኑ  በእጃቸው እንዲነኩት ወይም እንዲይዙት የሚፈቀድላቸው በፊፋ የተመረጡ ግለሰቦች፣ የውድድሩ አሸናፊ ቡድኖች አባላት እና የሀገራት መሪዎች ብቻ ናቸው። 

ከ 500 በላይ የመጠጥ አይነቶችን ከ 200 በላይ ሀገሮች ለሚገኙ ደምበኞቹ የሚያቀርበው ግዙፉ የለስላሳ መጠጥ አምራች ኮካኮላ የረጅም ጊዜ የፊፋ አጋር ሲሆን ከ 1978 አንስቶም የፊፋ አለም ዋንጫ የክብር አጋርነትን ተቆናጦ ያለ ነው።

ታሪካዊው ዋንጫ ከስምንት አመታት በፊት ከደቡብ አፍሪካው የ 2010 አለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ወደሀገራችን መጥቶ የአንድ ቀን ቆይታን አድርጎ መመለሱ አይረሳም። 

Advertisements