ጭምጭምታ / የዴቪድ ዴይኻ ወደማድሪድ የማምራት ነገር አይቀሬ መሆኑ ተገለፀ

የቀድሞው የሊቨርፑል ተጫዋች እና የአሁኑ የጨዋታ ተንታኝ ክሬግ ቤላሚ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ዴቪድ ዴይኻ ማንችስተር ዩናይትድን ለቆ ሪያል ማድሪድን መቀላቀሉ እንደማይቀር እምነቱን ገልጿል።

የአምናው የቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ማድሪድ ለአመታት ስሙ በከተማ ከተወለደው ዴይኻ ጋር ተያይዞ የቆየ ሲሆን ነሀሴ 2015 የዝውውር መስኮት መጠናቀቂያ የመጨረሻ ምሽት ላይም ተጫዋቹን በእጁ ለማስገባት ከጫፍ ደርሶ የወረቀት ስራዎች ብቻ ሳይጠናቀቁ በመስተጓጎላቸው ዝውውሩ ሳይሳካ ቀርቷል።

ቤላሚ ጉዳዩን በማስመልከት በሰጠው አስተያየትም የቀያይ ሴጣኖቹ ግብ ጠባቂ በመጪው የክረምት የዝውውር መስኮት ወደማድሪድ የመሄድ አጋጣሚውን አሻፈረኝ ለማለት በጣም እንደሚከብደው ተናግሯል።

“እሱ እውነተኛ ስምምነት ነው። እንደማስበውም ሪያል ማድሪድ ለአመታት ተጫዋቹን ቁጥር 1 በረኛው ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። እሱን የማግኘታቸው ነገርም የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው። 

“በእግሩ ሲጫወት አስደናቂ ነው፤ ግምታዊነቱም እንደዛ ነው። ወደፊት አርቆ ማሰብ የሚችል እና በእግሩ ብዙ ኳስ ማዳን የሚችል ነው። እሱ አስደናቂ ተጫዋች ነው። ወደእሱ እየገሰገሱ የሚመጡ አጥቂዎችን በትልቁ የሚፈትን ምርጥ ግብ ጠባቂ ነው።” ሲል ቤላሚ ሀሳቡን ሰጥቷል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ ያለው ማድሪድ በላሊጋው ከመሪው ባርሴሎና በ 19 ነጥቦች ርቆ አራተኛ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን የውጤት ቀውሱን ለመቅረፍም በመጪው ክረምት ትልልቅ ዝውውሮችን እንደሚፈፅም ይጠበቃል።

“በአብዛኛው ሁሉም ትልቅ የሚባል ክለብ እራሱን የሚያድስበት ጊዜ አለ። ምናልባት በማድሪድ ቤት ነገሩ ከባድ ይመስላል። ምክንያቱ ደግሞ በቻምፒዮንስ ሊጉ የነበራቸው ስኬት ነው። 

“ነገርግን ዴይኻ የለውጡ እና የዝውውር ወጪው ዋና ክፍል እንደሚሆን አስባለሁ። ማድሪድ በቅርብ አመታት ውስጥ ትልቅ ገንዘብ ለዝውውር አፍስሷል። ሁሌም እነሱ እንደዛ ናቸው። 

“ስለዚህ ዴይኻን ማስፈረም እና ከዩናይትድ መንጠቅ ትልቅ ገንዘብ ይጠይቃል። እሱ ወደዛ (ወደማድሪድ) ካላመራ ግን እኔ በጣም ድንጋጤ ውስጥ እገባለሁ።” ሲልም የዴይኻ ዝውውር የማይቀር እንደሆነ አፅንኦት በመስጠት ቤላሚ ሀሳቡን ቋጭቷል።

Advertisements