“ኮንቴ የሚለቁ ከሆነ አርሰናል በፍጥነት ሊቀጥራቸው ይገባል” – ፓል ሜርሰን

አንቶኒዮ ኮንቴ ቼልሲን የሚለቁ ከሆነ አርሰናል በፍጥነት ኮንቴን መቅጠር እንዳለበት የስካይ ስፖርት የእግር ኳስ ተንታኝ ፖል ሜርሰን ‘ዘ ዲቤት’ ለተሰኘው የእግር ኳስ ውይይት ፕሮግራም ተናገረ። 

ኮንቴ የአምናው የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሆነው ቢያጠናቅቁም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ያስመዘገቡት ውጤት በተለይም ደግሞ ከሰሞኑ በዋትፎርድ የደረሰባቸው የ 4-1 ሽንፈት የአሰልጣኝነት ወንበራቸውን ስጋት ውስጥ የከተተ ክስተት ሆኗል። 

አርሰን ቬንገር ባሳለፍነው የውድድር ዘመን የሁለት አመታት የውል ስምምነት የተፈራረሙ ቢሆንም ሜርሰን እንደሚለው ከሆነ ግን የፈረንሳዊው አለቃ የኢምሬትስ ቆይታ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊቋጭ ይችላል። 

“ኮንቴ ከቼልሲ በሚለቁበት ቀን እኔ የአርሰናል ሀላፊ ብሆን ቀጥታ ስልክ ላይ ነበር የምገኘው። እንደኮንቴ አይነት አሰልጣኞች ብቻቸውን አይመጡም። አርሰናል እንደሱ አይነት ሰዎችን ማበሳጨት የሚችል ሰው ያስፈልገዋል።

“ኮንቴ ሰዎችን ያበሳጫል። እሱ በሆነ መንገድ እንድትጫወት እና በኋላ መስመር ላይ ጠንካራ እንድትሆን ያስችልሀል። አርሰናል ከኋላ ክፍል ጠንካራ መሆን ከቻለ ሀያል ቡድን ይሆናል። 

“እንደማስበው አርሰናል ኮንቴን ‘በቀጣዩ አመት እናስፈርምህ በቃ’ ይሉታል። የማይሉት ከሆነ እነሱ አብደዋል ማለት ነው። አርሰናል እነዚህ ሁላ አሰልጣኞች ሊያልፉት አይገባም። 

“ጋርዲዮላ፣ ክሎፕ እና ጆሴ ሞውሪንሆን የመሰሉ አሰልጣኞች ቬንገር የአሰልጣኝነት ወንበሩን መልቀቅ ባለመቻላቸው ወደሌሎች ተፎካካሪ ቡድኖች ለመሄድ ተገደዋል።” በማለት ሜርሰን የሚሰማውን ተናግሯል።

ሜርሰን በመድፈኞቹ ማሊያ በነበረው የ 12 አመታት ቆይታ 327 ጨዋታዎችን አድርጎ 78 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ የአጥቂ አማካኝ ተሰላፊ ነበር።

Advertisements