“ልቤ አሁንም ያለው በማድሪድ ነው” – ቲቦ ኮርቱዋ

ቤልጅየማዊው የቼልሲ የግብ ዘብ ቲቦ ኮርቱዋ ከአገሩ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቆይታ በሰጣቸው ወደሪያል ማድሪድ የመዘዋወር ጉዳይ ሊሳካ የሚችል ነገር እንደሆነ የሚያሳብቁ ሃሳቦችን አንስቷል፡፡

በአትሌቲኮ ማድሪድ ለሶስት አመታት በውሰት በነበረው ቆይታ ወርቃማ ጊዜያትን ማሳለፍ ችሎ የነበረው ኮርቱዋ በኋላም ወደእናት ክለቡ ቼልሲ በመመለስ ፒተር ቼክን አስቀምጦ ዋነኛ ግብ ጠባቂ መሆን መቻሉ ይታወሳል፡፡

የ25 አመቱ ወጣት በድጋሚ ወደስፔን ተመልሶ ስለመጫወት በቀረበለት ጥያቄ “የግል ህይወቴ ከማድሪድ ከተማ ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው ፤ ባለቤቴና ሁለቱ ልጆቼ በከተማዋ እየኖሩ ነው፡፡ ትልቋ ልጄ በየቀኑ በማህበራዊ ሚዲያ በቪዲዮ ታወራኛለች፡፡ ታዲያ በየቀኑ የምትለኝ ‘ናፍቀኸኛል ‘ ነው ” በማለት የተረጋጋ ህይወትን ለማግኘት ሲል ወደማድሪድ ማቅናትን እንደሚሻ ተናግሯል፡፡

ተጫዋቹ ጨምሮም ” በየአጋጣሚዎቹ ክፍተት ሳገኝ ስፔን ደርሼ እመጣለሁ ፤ ሪያል ማድሪድ በኔ ላይ ፍላጎት ካለው ቼልሲን ቀርቦ ማነጋገር አለበት፡፡ ማድሪዶች እስካሁን ያንን አላደረጉም፡፡ ካደረጉ ግን የምናየው ይሆናል፡፡ ለማንኛውም ግን አሁን ከቼልሲ ጋር ውሌን ለማራዘም እየተደራደርኩ እገኛለሁ ” ብሏል፡፡

ከወደስፔን የሚመጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሎስ ብላንኮዎቹ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን በኮስታሪካዊው የክለቡ ቁጥር 1 ኬይለር ናቫስ ደስተኛ ቢሆንም ቡድኑን በወጣት ተጫዋቾች የመገንባት ዕቅድ አካል በሆነው መሰረት በዕድሜው ለጋ የሆነ ግብ ጠባቂን በሁለቱ ቋሚዎች መሃል ማሰለፍ ይሻል፡፡

Advertisements