“ኔይማርን ለማቆም ምንም አይነት ፎርሙላ አንጠቀምም” – ዳኒ ካርቭሀል

በቀጣይ ሳምንት የሚደረገው የአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቀው ከሪያል ማድሪድ እና ከፒ ኤስ ጂ ጨዋታ በፊት የማድሪዱ ተከላካይ ዳኒ ካርቭሀል ኔይማርን ለማቆም የሚጠቀሙት ፎርሙላ እንደሌለ አሳውቋል።

ሪያል ማድሪድ ከስፔን ላሊጋ እና ኮፓ ዴልሬ ውድድሮች መሰናበቱን ተከትሎ ትኩረቱን በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ለሁለት ተከታታይ አመት ባለ ትልቁን ጆሮ ዋንጫ ያነሱት ማድሪዶች በቀጣዩ ሳምንት ከፒ ኤስ ጂ ጋር ጠንካራ የጥሎማለፍ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል።

የፈረንሳዩ ክለብ በተረጋጋ መልኩ የፈረንሳይን ሊግ ኣ እየመራ የሚገኝ ሲሆን የአውሮፓ ንግስናን ማግኘት የመጀመሪያ ትኩረታቸው አድርገውታል።

ይህንን እቅዳቸውንም ለማሳካት ከፊትለፊታቸው የተቀመጠው የውድድሩ ገናና ቡድንን አሸንፎ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።

ለዚህ ደግሞ ትልቅ ሀላፊነት የወሰደው ኔይማር ሲሆን ከማድሪድ ጋር ሲጫወቱ ልዩነት ፈጥሮ ቡድኑን ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲሸጋገር የማድረግ ጫና ተሸክሞ ወደ ሜዳ ይገባል።

ኔይማር በሚጫወትበት የግራ መስመር ላይ ለማድሪዶች በቀኝ መስመር ላይ በመከላከል ብራዚላዊውን ኮከብ ለማቆም ያልታደለው ዳኒ ካርቭሀል በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ሆኗል።በቦታው ላይም ናቾ ወይንም አችራፍ ሀኪሚ እንደሚሰለፉ ይጠበቃል።

ከጨዋታው ቀደም ብሎም ካርቭሀል ማድሪድ ኔይማርን ለማቆም የተለየ ፎርሙላ እንደሌለው አሳውቋል።

“ከሁለቱ ተከላካዮች ማን እንደሚሰለፍ አላውቅም።ሁለቱም ለቦታው ብቁ ናቸው።ኔይማርንም ለመጋፈጥ ምንም አይነት ፎርሙላ አንጠቀምም።” ሲል ተናግሯል።

Advertisements