አቋም / አርትሮ ቪዳል ወደ ዩናይትድ እንደሚያመራ በሚናፈሰው ጭምጭምታ ዙሪያ ምላሽ ሰጠ

አርትሮ ቪዳል ወደ ማንችስተር ዩናይትድ እንደሚያመራ በሚናፈሰው ጭምጭምታ ዙሪያ በሰጠው ምላሽ ፍላጎቱ በባየር ሙኒክ መቆየት መሆኑን በመግለፅ ለክለቡ ያለው ታማኝነት ለማሳየት ጥረት አድርጓል።

በቺሊያዊው ተጫዋች ዙሪያ ቀያዮቹ ሴይጣኖች እና ሰማያዊዎቹ ቼልሲዎች ትልቅ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን ተጫዋቹ በውል ስምምነቱ ላይ 18 ወራት ብቻ የቀረው  መሆኑ ደግሞ ብዙ ክለቦች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አስገድዷቸዋል።

ነገርግን የቀድሞው የጁቬንቱስ ኮከብ በአሊያንዝ አሬና የመቆየት ፍላጎት እንዳለው ከስፖርት 1 ጋር ባደረገው ቆይታ ላይ ተናግሯል።

ቪዳል ሲናገር “እኔ ስለዝውውር አላስብም። እዚህ በጣም ተመችቶኛል። በእርግጥም የውል ስምምነቴን የማራዘም ፍላጎት አለኝ። ያ አማራጭ ነው። ልጆቼ እዚህ በመሆናቸው በጣም ደስተኛ ናቸው።” በማለት አቋሙን አሳውቋል።

ቪዳል በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለክለቡ ባየር ሙኒክ 18 ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። 

Advertisements