ቼልሲን በጥር የዝውውር መስኮት ለቆ ወደ ጀርመኑ ክለብ ቦርሲያ ዶርትመንድ በውሰት ውል ያቀናው ቤልጄማዊው ኮከብ ሚኪ ባቱሻይ ገና ከወዲሁ የጀርመኑን ክለብ ደጋፊዎች እያስደሰተ ይገኛል፡፡ በሁለት ጨዋታዎች ሶስት ግቦች አስቆጥሮ 1 ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ በማቀበልም በሲግናል ኤዱና ፓርክ ማንጸባረቁን ቀጥሏል፡፡
ቦርሲያ ዶርትሙንድም የጋቦናዊውን አጥቂ ፔየር ኤምሪክ ኦውባሚያንግ ወደ አርሰናል ማቅናት ተከትሎ የእርሱ አልጋ ወራሽ በመሆን የመጣውን ቤልጄማዊውን ግብ አዳኝ በቋሚነት ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየቱን ኢቭኒንግ ስታንዳርድ አስነብቧል፡፡ በዝውውሩ መገባደጃ ሰዓት በውሰት ውል ቼልሲን ለቆ የጀርመኑን ክለብ ሲቀላቀል ዶርትሙንድ በስምምነቱ ላይ ተጫዋቹን በክረምት ከፈለጉት በቋሚነት የማስፈረም እድል እንዲኖራቸው አንቀጽ ቢያካትቱም ጥያቄው በቼልሲ ቤት ውድቅ ሆኗል፡፡
ሰለ ሚኪ ባቱሻይ ኮንትራት ከቢልድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክለቡ ሊቀ መንበር ሃንስ ጆኣኪም ዋትዘ “ሁሌም እርሱን የማስፈረም እድል አለን ሆኖም እርሱ በየጊዘው ግብ ማስቆጠሩን ከቀጠለ ዝውውሩን ከባድ ያደርግብናል” ሲሉ ቀልድ አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ቼልሲን በ2016 ከፈረንሳዩ ክለብ ማርሴይ በ33 ሚሊየን ፓውንድ የተቀላቀለው ሚኪ ባቱሻይ በሰማያዊዎቹ ቤት የተጠበቀውን ያህል በዚህ የውድድር ዘመን ባያገለግልም በሁሉም ውድድሮች ላይ 10 ግቦችን ማስቆጠር ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ቼልሲም ከአርሰናል ፈረንሳዊውን አጥቂ ኦሊቪየር ጅሩድን በ18 ሚሊየን ፓውንድ ማስፈረሙን ተከትሎ ክለቡን በውሰት ውል ለቋል፡፡