ትግል / አትሌቲኮ ማድሪድ በዩናይትድ እና ማድሪድ የሚፈለገውን የ 21 አመቱን ጀርመናዊ ኮከብ ለማስፈረም የዝውውር ፉክክሩን መቀላቀሉ ተገለፀ

አትሌቲኮ ማድሪድ የአርቢ ሌፕዚኩን አጥቂ ቲሞ ዌርነርን ለማስፈረም ከሌሎቹ ፈላጊዎቹ ማንችስተር ዩናይትድ እና ሪያል ማድሪድ ጋር ለመቀናቀን ፉክክሩን መቀላቀሉ ተገለፀ።

ሰዘን የጀርመኑን ስፖርት ቢልድ እማኝ አድርጎ እንደፃፈው አትሌቲኮ በ 21 አመቱ ተጫዋች ላይ ፍላጎት ማሳደሩን ባሳበቀ መልኩ ቡድኑ በሳምንቱ መጨረሻ አግስበርግን 2-0 በረታበት ጨዋታ መልማይ ልኮ ተመልክቶታል።

የሌፕዚኩ ዳይሬክተር በበኩላቸው በተለያየ ጊዜ ዌርነር እንደማይሸጥ “እሱን ከእኛ ጋር እናቆየዋለን። ከወኪሉ ጋር ከባድ ድርድር ላይ ነን።” ሲሉ ተናግረው የክለባቸውን አቋም ማሳወቃቸው አይረሳም።  

ነገርግን ከጀርመን እየወጡ ያሉ መረጃዎች የተጫዋቹን የውል ስምምነት ከ 2020 ለማሻገር የሚደረገው ድርድር መቆሙን እና መጪው አለም ዋንጫም በተጫዋቹ ላይ ይበልጥ ትኩረት እንዲያርፍበት እንደሚያደርግ እየጠቆሙ ይገኛል።

የውል ማፍረሻ ሂሳቡ 86 ሚሊዮን ፓውንድ የሆነው ዌርነር በባርሴሎና ጭምር የሚፈለግ ቢሆንም በልጅነቱ የዩናይትድ ደጋፊ እንደነበርና አንድ ቀን ለኦልትራፎርዱ ክለብ የመጫወት ፍላጎት እንዳለው ማመኑ ተያይዞ ተገልጿል።

ዌርነር በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች ላይ 12 ግቦችን ሲያስቆጥር በመጪው አለም ዋንጫም በጀርመን ስብስብ ውስጥ ቦታ ማግኘቱ እርግጥ ይመስላል።

በሌላ በኩል ግን ባሳለፈው መስከረም ወር ዌርነር ቡድኑ ከቱርኩ ቤሽኪሽታሽ በነበረው የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ በስታዲየሙ በነበረው ከፍተኛ ድምፅ የተነሳ የጆሮ ህመም ስለተሰማው ጨዋታውን በ 30ኛው ደቂቃ አቃርጦ ለመውጣት ተገዷል። 

በወቅቱ ዌርነር ለድምፅ መከላከያ የጆሮ ማዳመጫ እስኪሰጠው ድረስም እጁን ጆሮ ውስጥ በመክተት ድምፁን ለመከላከል ሲጥር የታየ ሲሆን ከጆሮ ህመሙ በተጨማሪም የደም ዝውውር እና የአተነፋፈስ ችግር እንዳለበትም ሲነገር ነበር።

ከዚህ ችግሩ ጋር በተያያዘም ማድሪድ ጀርመናዊውን ተስፈኛ ለማስፈረም የነበረውን እቅድ በመሰረዝ ዌርነርን ሊያስፈርም እንደማይፈልግ መዘገቡ ይታወሳል። 

Advertisements