ሪከርድ / ሀሪ ኬን በቻምፕየንስ ሊጉ የስቴቨን ጄራርድን ሪከርድ ተጋራ

​እንግሊዛዊው የስፐርሱ አጥቂ ሀሪ ኬን በቻምፕየንስ ሊጉ ጁቬንቱስ ላይ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ስቴቨን ጄራርድ ይዞት የነበረውን ሪከርድ ተጋርቷል።

የአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ 16 ቡድኖች የሚያደርጉት የጥሎማለፍ ጨዋታ ሲጀመር ተጠባቂ የነበረው የጁቬንቱስ እና የስፐርስ ጨዋታ በአቻ ውጤት 2-2 ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ ጁቬንቱሶች ቀድመው በጎንዛሎ ሂግዌን ሁለት ጎሎች ድንቅ አጀማመር ቢያደርጉም በእንግሊዙ ቡድን ተበልጠው መሪነታቸውን ማስጠበቅ ሳይችሉ ወጥተዋል።

ለእንግዳዎቹ ደግሞ ጎል በማግባት አስገራሚ ሪከርድ እየሰራ ያለው ሀሪ ኬን አልደፈር ያለውን የጁቬንቱስ የሜዳው ላይ ጠንካራ ጎል ሳይቆጠርባቸው የመውጣት ሪከርድ ማብቂያውን አበጅቶለታል።

አሮጊቷ በሜዳዋ ያደረገችው ጨዋታ ጎል ያስተናገደችው ከ 826 ደቂቃ በኋላ ሲሆን አግቢውም እንግሊዛዊው ሀሪ ኬን ሆኗል።

ኬን በአስገራሚ ብቃት ያስቆጠራት ጎል ስፐርሶችን ይበልጥ ያነቃቃች ስትሆን የተጫዋቹም ብቃት እየተወደሰ ይገኛል።

ይህም ዘንድሮ በቻምፕየንስ ሊጉ ያስቆጠራቸው የጎል ብዛት ሰባት እንዲደርስ አድርጎታል።

የጎል መጠኑ ደግሞ አንድ እንግሊዛዊ በአንድ የቻምፕየንስ ሊግ የውድድር አመት ያስቆጠረው ከፍተኛው የጎል ቁጥር ጋር ተስተካክሏል።

2008/2009 ላይ የቀድሞ የሊቨርፑሉ አማካይ ስቴቨን ጄራርድ በዛን አመት የተካሄደው የቻምፕየንስ ሊግ ውድድር ላይ ሰባት ጎሎችን በማስቆጠሩ በአንድ የውድድር አመት በቻምፕየንስ ሊጉ ከፍተኛ ጎል በማስቆጠር ብቸኛ እንግሊዛዊ ነበር።

ከምሽቱ ጨዋታ በኋላ ግን የጎል ሪከርዱን ሀሪ ኬን ተጋርቶታል።ተጫዋቹ ቡድኑ ከውድድሩ ባለመሰናበቱ በቀጣይ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ጎል ማስቆጠር የሚችል ከሆነ ሪከርዱን ብቻውን የሚይዝ ይሆናል።

ተጫዋቹ በሳምንቱ መጨረሻም በተመሳሳይ በእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ የከተማቸውን ባላንጣ የሆነውን አርሰናልን ሲያሸንፉ ድንቅ የጭንቅላት ኳስ በማስቆጠር በጎረቤታቸው ላይ የበላይነት እንዲወስዱ መርዳት እንደቻለ ይታወሳል።

Advertisements