ሪከርድ/ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊቨርፑል አዲስ ሪከርድ አስመዘገቡ

የአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ የጥሎማለፍ ጨዋታዎች ቀጥለው ሲካሄዱ የማድሪዱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና የእንግሊዙ ሊቨርፑል አዲስ ሪከርድ አስመዝግበዋል።

እጅግ ተጠባቂ የነበረው ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ብልጠት በታከለበት መንገድ የማታ ማታ ፒ ኤስ ጂን 3 -1 ማሸነፍ ችሏል።

በሳንቲያጎ በርናባው በተደረገው ጨዋታ እንግዳዎቹ ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን አግቢውም አድርያን ራቦት ነበር።

ከጎሉ በኋላ ተደናግጠው የነበሩት ማድሪዶች ከእረፍት በፊት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሮናልዶ በማስቆጠር አቻ መሆን ችለዋል።

ከእረፍት መልስ የተሻሉ የነበሩት ፔዤ ተደጋጋሚ ጎል የማስቆጠር እድል ቢያገኙም ሳጥን ውስጥ ደካማ ስለነበሩ የማታ ማታ ሁለት ጎል አስተናግደው 3-1 ተሸንፈዋል።

በእለቱ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ሮናልዶም በአጠቃላይ በአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ ላይ 115 ጎሎችን ሲያስቆጥር በማድሪድ ብቻ ደግሞ 100ኛ ጎሉ ነው።

ይህ ደግሞ በውድድሩ በአንድ ክለብ ውስጥ አንድ ተጫዋች ያስቆጠረው ትልቁ የጎል መጠን በመሆን ሮናልዶ አዲስ ሪከርድ ጨብጧል።

ወደ ፖርቹጋል ያቀናው ሊቨርፑል ደግሞ ጨዋታውን ጨርሶ ተመልሷል።ከሜዳው ውጪ ፖርቶን 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል።

ይህ የጎል መጠን ደግሞ አንድ የእንግሊዝ ክለብ በአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ የጥሎማለፍ ጨዋታ ላይ ከሜዳው ውጪ ያስመዘገበው ትልቁ ውጤት ሆኗል።

የሪከርዱ ባለቤት የነበረው ማን ሲቲ ማክሰኞ ባዘልን 4-0 ያሸነፈበት ትልቁ ውጤቱ የነበረ ቢሆንም ከ 24 ሰአት በኋላ በሊቨርፑል ሪከርዱን ተነጥቋል።

Advertisements