ጄረርድ፡ ይህኛው የሊቨርፑል የፊት መስመር በስዋሬዝ ይመራ ከነበረው የተሻለ ነው

እንደስቴቨን ጄራርድ ሃሳብ ከሆነ ሊቨርፑል በዚህ የውድድር ዘመን ስዋሬዝ የፊት መስመሩን በኮከብነት ከመራበት ጊዜ የተሻለ አጥቂ አለው።

የየርገን ክሎፑ ሶስት ተጫዋቾችን የያዘው አስደናቂ የፊት ክፍል ረቡዕ ምሽትም 16 ክለቦች በሚሳተፉበት የሻምፒዮንስ ሊግ የደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ጨዋታ ፓርቶን 5ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ድል በማድረግ ዳግመኛ አስደናቂ ብቃቱንን ማሳየት ችሏል።

ሊቨርፑል ወደሩብ ፍፃሜ ለማልፍ የሚችልበትን ዕድል ማስፋት በቻለበት በዚህ ጨዋታ ሳዲዮ ማኔ ሃትሪክ መስራት ሲችል፣ መሐመድ ሳለህና ፊርሚኖ ቀሪዎቹን ግቦች አስቆጥረዋል።

ሶስቱ የፊት ተጫዋቾች በዚህ የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች በጥምረት 63 ግቦችን አስቆጥረዋል። እናም ጄራርድ የአሁኑ አጥቂዎች በ2013-14 የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማሸነፍ ተቃርቦ ከነበረውና ልዊስ ስዋሬዝን፣ ዳንኤል ስተሪጅን እና ራሂም ስተርሊንግን ከያዘው የአጥቂ ክፍልም እንደሚልቁ ያስባል።

“ሁለቱም እጅግ ጥሩ ናቸው። በስዎሬዝ በሚመራው እና በዚህኛው ቡድን መካከል ስላለውን ንፅፅር የምለው ነገር አሁን ጥሩ ጥምረት ያለ ስለመሆኑ ነው።” ሲል ጄራርድ ለቢቲ ስፖርት ተናግሯል።

“በማኔ ፍጥነትና ቀጥተኛ አጨዋወት ይኖርሃል። በፈርሚኖ ደግሞ የኳስ ቅብብል እና ኳስን ይዞ መጫወትና ኳስን በሚገባ ማስጠበቅ ትችላለህ። እንዲሁም ሳልን ይዘህ የግብ ዕድል ማመቻቸትና ግብ ማስቆጠርን በአንድ ላይ መፈፀም ትችላለህ።

“ውህደቱ ድንቅ ነው።”

ሊቨርፑል በፕሪሚየር ሊጉ ማንችስተር ሲቲን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ሲያጠናቅቅ ጄራርድ በስዋሬዝ ከሚመራው ሶስቱ የፊት ተጫዋቾች ጀርባ ሆኖ ተጫውቷል።

የ37 ዓመቱ ተጫዋች የአሁኑን ስብስብ የቡድን ስራ ሲያወድስ “የዚህኛው ሊቨርፑል ቡድን የስራ ጥረት በጣም በጣም ልዩ ነው፤ ምን ያህል ራስወዳድ እንዳልሆነም ልትገነዘብ ትችላለህ።

“በቡድኑ ውስጥ ስግብግብነት የለም። ራስ ወዳድ የሆነም ማንም የለም። እርስ በርሳቸው ኳስን ይቀባባሉ።

“አንድ ሰው ጥሩ ቦታ ላይ ከተገኘ እርስ በእርስ በመተያየት ወደውሳኔ ይገባሉ። ምክኒያቱም በጣም ብዙ እንደሚያስቆጥሩ ያውቁታል።” ሲል ገልፅዋል።

Advertisements