ሹመት/ አሌክስ ማክሊሽ የስኮትላንድ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

የስኮትላንድ እግርኳስ ማህበር የቀድሞውን የበርኒንግሀም እና አስቶንቪላ አሰልጣኝ የነበሩትን የ59 አመቱን አሌክስ ማክሊሽን የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን አሳውቋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2007 የስኮትላንድ ብሄራዊ ቡድን በአሰልጣኝነት መርተው ለ2008  የአውሮፓ ዋንጫ ማሳለፍ ያልቻሉት አሌክስ ማክሊሽ ጎርዳን ስትራካንን ተክተው ብራዊ ቡድኑን የተረከቡ ሲሆን  የመጀመሪያ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታቸውንም ማርች 23 በሀምፕደን ፓርክ ከኮስታሪካ ጋር የሚያደርጉ ይሆናል፡፡

̋የስኮትላንድ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ተብሎ  መሾም ታላቅ ክብር ነው ይህንን እድል ዳግም በማግኘቴ ኩራት ተሰምቶኛል ሲሉ ብሄራዊ ቡድኑን ለሁለተኛ ጊዜ መያዛቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡˝

አሌክስ ማክሊሽ በስኮትላንድ እግር ኳስ ታሪክ በርካታ ጨዋታዎችን በማድረግ 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻሉ ሲሆን በሶስት የአለም ዋንጫ ውድድሮች ላይም ተካፍለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በክለብ ደረጃ ለስመ ጥሩ ክለብ አበርዲን ከ700 በላይ ጨዋታዎችን አድርገው የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫን ጨምሮ 13 ድሎችን አሳክተዋል፡፡

በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በ2002/2003 የውድድር ዘመን ከሬንጀርስ ጋር የስኮቲሽ ሊግ ዋንጫን ያሳኩ ሲሆን በ2011 በዌምብሌይ በተደረገው የካርሊንግ ካፕ ፍጻሜ ጨዋታም በርሚንግሀምን ይዘው አርሰናልን 2-1 በማሸነፍ ዋንጫውን ከፍ ማድረግ ችለዋል፡፡

Advertisements