ጆሴ ሞሪንሆ ኤሪክ ቤሊ በ ኤፍ ኤ ካፑ ጨዋታ ላይ እንደሚመለስ አሳወቁ

የማንችስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ተከላካያቸው ኤሪክ ቤይ ነገ ለሚያደርጉት የኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታ ላይ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ አሳውቀዋል።

ክሪስ ስሞሊንግ እና ፊል ጆንስ እያሳዩ ያሉት ደካማ እንቅስቃሴ በማንችስተር ዩናይትድ ያላቸው ቆይታ በክረምቱ የዝውውር መስኮት እንደሚያበቃ ጠንከር ብሎ መሰማት በጀመረበት ወቅት ሌላው ተከላካያቸው ኤሪክ ቤሊ ወደ ሜዳ መመለሱ ለደጋፊዎች እረፍት ሆኗል።

ሁለቱ ተጫዋቾች በክለቡ ትንሽ የማይባል አመታትን መቆየት ቢችሉም እድገታቸው ግን ከመሻሻል ይልቅ ቁልቁል መጓዝ ሆኗል።

ከፉልሀም እና ከብላክበርን ወደ ዩናይትድ የተዘዋወሩት ስሞሊንግ እና ጆንስ ትልቅ ተስፋ ተሰንቆባቸው ቢቆዩም በተለይ በቅርቡ እያሳየዩ የሚገኙት በስህተት የታጀበ እንቅስቃሴ ከክለቡ ጋር መለያየታቸው መቃረቡ እየተነገረ ይገኛል።

የስሞሊንግ እና የጆንስ ጥምረት በተደጋጋሚ ለመመልከት ተገደው የነበሩት ጆሴ ሞሪንሆ ሌላኛው ተከላካይ ኤሪክ ቤሊ ከጉዳት መመለሱ መልካም ዜና ሆኖላቸዋል።

በተለይም በቀጣይ ሳምንት ከሚያደርጉት የቻምፕየንስ ሊጉ ጨዋታ በፊት አይቮሪኮስታዊው ተከላካይ ወደ ሜዳ መመለሱ የቡድኑን የተከላካይ ክፍልን እንደሚያጠናክረው ይታሰባል።

ቤሊ ለቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወተው ዩናይትዶች በቼልሲ 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ሲሆን በቁርጭምጭሚት ጉዳት አጋጥሞት ላለፉት ረጅም ሳምንታት ከጨዋታ ውጪ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።

ዩናይትዶች ቅዳሜ ምሽት ከኸደርስፊልድ ጋር በኤፍ ኤ ካፕ የሚጫወቱ ሲሆን በዚህ ጨዋታ ላይ ኤሪክ ቤሊ በጨዋታው ላይ ለመሰለፍ ብቁ መሆኑን ጆሴ ሞሪንሆ አሳውቀዋል።

Advertisements