ኤርኔስቶ ቫልቬርዴ ቼልሲ በቻምፕየንስ ሊጉ ከባርሴሎና የተሻለ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል አሳወቁ

ቼልሲ ባርሴሎናን በሚያስተናግድበት የማክሰኞ ምሽቱ የቻምፕየንስ ሊጉ ፍልሚያ ላይ ባለሜዳዎቹ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ የባርሴሎናው አሰልጣኝ ኤርኔስቶ ቫልቬርዴ ገልፀዋል።

ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ውጤት ያጡበትን ያለፉት ተከታታይ ሳምንታት ወቅት መርሳት የቻሉት ቼልሲዎች በአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊጉ የስፔኑን ባርሴሎናን ያስተናግዳሉ።

ተጠባቂው ጨዋታ ማክሰኞ ምሽት የሚደረግ ሲሆን ባለሜዳዎቹ ትናንት ምሽት የኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታ ከተጫወቱ በኋላ ሙሉ ትኩረታቸውን በቻምፕየንስ ሊጉ ጨዋታ ላይ አድርገዋል።

ባርሴሎናዎች ደግሞ የላሊጋ ጨዋታቸውን ቅዳሜ አመሻሹ ላይ የሚጫወቱ በመሆኑ ከቻምፕየንስ ሊጉ ጨዋታ በፊት ትኩረታቸውን በሀገራቸው ሊግ ላይ አድርገዋል።

ይህ የጨዋታ ቀን ልዩነት ደግሞ ቼልሲዎች ከባርሴሎና ይልቅ የአንድ ቀን የማገገሚያ የእረፍት ቀን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።

እንደ ባርሴሎናው አሰልጣኝ ኤርኔስቶ ቫልቬርዴ ሀሳብ ከሆነ ቼልሲ ያገኘው የአንድ ቀን ተጨማሪ የማገገሚያ የእረፍት ቀን ተጠቃሚ ሊያደርገው እንደሚችል ነው።

“በአካል ደረጃ የማገገሚያ ጊዜ ለማግኘት የአንድ ተጨማሪ ቀን ልዩነት አለን።እኛም ከቼልሲ ጨዋታ በፊት ተጨማሪ የማገገሚያ ቀን ለማግኘት ከአይባር ጋር አርብ ብንጫወት እንወድ ነበር።

“ነገርግን የአይባር ጨዋታ እራሱ አስፈላጊያችን ነው።በአሁን ሰአት ብቸኛ የምናስበው ጨዋታ የአይባሩ ነው።ስለ ማክሰኞው የቻምፕየንስ ሊጉ ጨዋታ እያሰብን አይደለም።”በማለት ቼልሲ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

ባርሴሎና ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የሚያደርገው ጨዋታ ላይ ቁልፍ ተጫዋቾቹን እንደሚያሳርፍ ይጠበቃል።

Advertisements