“ፖል ፓግባ የሪያል ማድሪድ የዝውውር ኢላማ አይደለም” – ሂሌም ባላጉ


የማንችስተር ዩናይትዱ አማካኝ ፖል ፖግባ በሪያል ማድሪድ ኢላማ ውስጥ እንደወደቀ የሚወጣው ዘገባ ሀሰት መሆኑን ብዙ ጊዜያት የተናገረው የሚሰምርለት ስፔናዊው ጋዜጠኛ ሂሌም ባላጉ ገለፀ።

ጆሴ ሞውሪንሆ ፈረንሳዊውን አማካኝ ቡድናቸው በቶትነሀም እና ኒውካስትል በተሸነፈበት ወቅት ቀይረው ያስወጡት ሲሆን ሀደርስፊልድን በረቱበት የኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ደግሞ ተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጠውት ታይተዋል።

ሞውሪንሆ በውድ የዝውውር ሂሳብ ያመጡትን ፓግባ በተገቢው መንገድ ካለመያዛቸው ጋር በተገናኘ ቀጣይ የእግር ኳስ ህይወቱ ከኦልትራፎርድ ውጪ እንደሆነ የሚወራው ሀሰት መሆኑን ባላጉ ተናግሯል።

ባለጉ ሲናገር “አንድ በትልቅ ክለብ የሚገኝ ኮከብ ተጫዋች ዙሪያ ነገሮች በጥሩ መንገድ እየተጓዙ ካልሆነ በሚዲያ ላይ የሚወሩ ጭምጭምታዎች መፈጠር መጀመራቸው የተለመደ ነው። 

“በፖግባ ዙሪያ በፈረንሳዩ ጋዜጣ ያፈተለከ አንድ መረጃ ሌኪፕ ተጫዋቹ በሜዳ ላይ የሚያሳየውን ብቃት ለማሻሻል በተለየ ስፍራ ላይ መጫወት መፈለጉን አትቷል። እንደዛ አይነት መረጃዎች ሲወጡ አትገረሙ። ማድሪድ እንደሚፈልገው የሚገልፅ መረጃ መውጣቱ የሚጠበቅ ነበር። 

“ነገርግን ማድሪድ አያደርገውም። እነሱ በዚህ ክረምት ዋነኛ ኢላማቸውን ከገዙ በኋላ ፖግባን መግዛት የሚያስችል ገንዘብ አይኖራቸውም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የማድሪድ ፕሬዝዳንት እሱን እንደ ዝውውር ኢላማ አይመለከቱትም።”  ብሏል።

ባላጉ በንግግሩ የማድሪድ ቀዳሚ የዝውውር ኢላማዎች የሚሆኑት ኤደን ሀዛርድ እና ቲቤት ኮርትዋ አሊያም ደግሞ ዴቪድ ዴይኻ እንደሚሆኑ ግምቱን ይፋ አድርጓል። 

ከዚህ በተጨማሪም የስፔኑ ክለብ በመጪው ክረምት ተጨማሪ ዝውውሮችን የሚያደርገው በቀሪው የውድድር ዘመን ወይም በመጪው አለም ዋንጫ ላይ ድንቅ ብቃታቸውን ሊያሳዩ ከሚችሉ ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ እንደሆነ ጨምሮ አስረድቷል።

Advertisements