ፔፕ ጓርዲዮላ በተጨዋችነት ዘመኑ ለዊጋን አትሌቲክ ያልፈረመበት ምክንያት አሳወቀ

​የማን ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ጫማ ከመስቀሉ በፊት በእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ለዊጋን አትሌቲክ  ለመፈረም ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ዝውውሩ ያልተሳካበት ምክንያት ተናግሯል። 

ፔፕ ጓርዲዮላ ጫማ ከመስቀሉ በፊት በእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ የመጫወት ፍላጎቱን ለማሳካት አልቻለም።

2005 ላይ እድሜው 34 ደርሶ በነፃ ዝውውር ወደ እንግሊዝ አቅንቶ ለዊጋን አትሌቲክ ለመፈረም ቢቃረብም ሳይሳካለት ቀርቷል።

የዛን ወቅት የዊጋን አሰልጣኝ የነበሩት ፖል ጂዌል ለቡድናቸው የአማካይ ተጫዋች ለማስፈረም ፔፕን ቢያስቡም ለቡድኑ ብቁ አይደለም በማለት ሀሳባቸውን ቀይረዋል።

ከኳታሩ አል አህሊ ከለቀቀ በኋላ ክለብ አልባ የነበረው ፔፕ ከዊጋኑ አሰልጣኝ ጋር በስልክ ጭምር ቢነጋገሩም በመጨረሻ ላይ ግን ዝውውሩ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግሯል።

ወቅቱን የሚያስታውሰው ፔፕ ጓርዲዮላ “የእንግሊዝ እግርኳስ ለመጫወት ወደ እዚህ ለመምጣት ሞክሬ ነበር ነገርግን የእውነት አርጅቼ ስለነበር ጥሩ ተጫዋች አልነበርኩም።”ሲል ያስታውሳል።

ማን ሲቲ በኤፍ ኤ ካፕ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት ምሽት ላይ ከዊጋን ጋር የሚጫወት ይሆናል።

Advertisements