ምርመራ / ማንችስተር ሲቲ በሰርጂዮ አግዌሮ የምሽቱ ሁነት ዙሪያ ክስ ለማቅረብ ነገሮችን እያጤነ እንደሆነ ተገለፀ

ማንችስተር ሲቲ በትናንት ምሽቱ ጨዋታ ላይ በዊጋን ደጋፊዎች መሰደቡን እና የምራቅ መተፋት ጥቃት እንደደረሰበት የገለፀውን ሰርጂዮ አግዌሮ በሚመለከት ክስ ለማቅረብ ነገሮችን እያጤነ መሆኑ ተገለፀ። 

ከኤፍኤ ዋንጫው አምስተኛ ዙር የተሰናበተው ሲቲ በዲደብሊው ስታዲየም ከተፈጠረው አጋጣሚ ጋር በተያያዘ በዛሬው ዕለት ረፋድ ከአርጀንቲናዊው አጥቂ ጋር ንግግር አድርጓል። .

በምሽቱ ጨዋታ መጠናቀቂያ ላይ ደጋፊዎች ወደሜዳ ዘለው መግባታቸውን ተከትሎ የታላቁ ማንችስተር ፖሊስ ክፍል፣ የዊጋን አትሌቲክስ ክለብ እና የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ሁነቱን በተመለከተ የማጣራት ስራ እየከወኑ ይገኛል።

አግዌሮ በወቅቱ ከደጋፊዎች ጋር ሲጣላ የታየ ሲሆን ትንኮሳና በአንድ የዊጋን ደጋፊ ምራቅ የመተፋት ጥቃት እንደደረሰበት አስታውቋል።

የእንግሊዙ ስካይ ስፖርት ምንጮቹን ጠቅሶ እንደፃፈውም የኢትሀዱ ክለብ በአጥቂው ላይ የተለመደ አይነት የስድብ ትንኮሳ እንደተፈፀመበት እያጣራ መሆኑ ተነግሯል። 

ከዚህ በተጨማሪም ሲቲ በዊጋን ስታዲየም በነበሩት አስተናባሪዎች ደስተኛ እንዳልነበር እና ሜዳው በደጋፊዎች በተወረረበት ወቅትም በቂ እርምጃ እንዳልወሰዱ ማሰቡን ተያይዞ ተወስቷል።

Advertisements