ሲቪያ ከ ዩናይትድ / ጉዳት ላይ የነበሩ አብዛኛዎቹ የዩናይትድ ተጫዋቾች ከነገ ምሽቱ ፍልሚያ በፊት ወደ ልምምድ ተመለሱ

ፓል ፖግባና ዝላታን ኢብራሂሞቪች ከነገ ምሽቱ የሲቪያ የ 16ቱ ቡድኖች ፍልሚያ በፊት ወደልምምድ ተመልሰዋል። 

ከሁለቱ የዩናይትድ ኮከቦች በተጨማሪ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከሀደርስፊልድ በነበረውና የኦልትራፎርዱ ክለብ 2-0 በሆነ ውጤት ባሸነፈው የኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ አምስተኛ ዙር በቡድኑ ያልነበሩት አንደር ሄሬራ፣ ማርከስ ረሽፎርድ እና አንቶን ቫሌንሲያ ወደልምምድ ከተመለሱት መሀከል ናቸው። 

ከዚህ ቀደም የዩናይትዱ አለቃ ጆሴ ሞውሪንሆ የቅዳሜው ጨዋታ በህመም ያመለጠው ፖግባ ወደ ስፔን ከሚደረገው ጉዞ ውጪ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም አስተያየትን ሰጥተው ነበር።

ኢብራሂሞቪች በበኩሉ በቦክሲንግ ዴይ ፍልሚያ ዩናይትድ ከበርንሌይ 2-2 አቻ በተለያየ ጨዋታ ከደረሰበት ጉዳት ጋር በተያያዘ እስካሁን ወደሜዳ መግባት አልቻለም። 

በሀደርስፊልዱ ጨዋታ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ የተሰለፈው አይቮሪኮስታዊው ኤሪክ ቤሊ ደግሞ በካሪንግተን ተገኝቶ ልምምድ የሰራ ሲሆን በነገው ምሽት ጨዋታም ወደሜዳ ሊመለስ ይችላል። 

በሌላ በኩል ማርከስ ሮሆ፣ ማርዋን ፌላኒ እና ፊል ጆንስ በጉዳት ምክንያት የረቡዕ ምሽቱ ጨዋታ እንደሚያመልጣቸው ተነግሯል። 

Advertisements