ሲቪያ ከ ማንችስተር ዩናይትድ | የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ

ማንችስተር ዩናይትድ ረቡዕ ምሽት ሲቫያን ለመግጠም ወዳስታዲዮ ራሞን ሳንቼዝ ፒዥዋን በመጓዝ ከአራት የውድድር ዘመን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ይመለሳል።

ማንችስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት ኸደርስፊልድን በእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ዋንጫ 2ለ0 በመርታት እና ለሩብ ፍፃሜው ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ አስደሳች ስሜት ውስጥ በመሆን ይህን የረቡዕ ምሽቱን ጨዋታ ያደርጋል።

በሌላ በኩል ባለሜዳው ሲቪያ በውጤት ማጣት ችግር ውስጥ የሚገኘውን ላስ ፓልማስን ከሜዳው ውጪ 2ለ1 በመረታት በላ ሊጋው ደረጃውን ወደአምስተኛ ከፍ ማድረግ ችሏል።

ሲቪያ በዚህ የውድድር ዘመን ከገና በዓል በፊት በምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ከሊቨርፑል ጋር በሁለት ጨዋታዎች ላይ አዝናኝ በሆነ ሁኔታ በአቻ ውጤት መለያየት የቻለ ሲሆን በአውሮፓ መድረኮች ላይም ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር በነበረው የቀደሙ ጨዋታዎች መልካም የሚባሉ ናቸው።

የቡድኖቹ ዜናዎች

ሲቪያ በቋንጃ ጉዳት ላይ ይገኝ የነበረው የጨዋታ አቀጣጣዩ ኤቨር ባኔጋ በዚህ ሳምንት ልምምድ የጀመረለት ሲሆን፣ የክንፍ ተጫዋቹ ዡዋኪን ኮሬያም በዚህ ጨዋታ ላይ የመሰለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።

የቀሞው የማንችስተር ሲቲ የክንፍ ተጫዋች ኖሊቶም ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ ካራቀው ጉዳት ተመልሶ ልምምድ መስራት የጀመረ በመሆኑ በምሽቱ ጨዋታ ላይም የመሰለፍ ሚና ሊኖረው ይችላል።

የዩናይትድ ሁለት ተጫዋቾች፣ ማርከስ ራሽፎርድ እና አንደር ሄሬራ በጉዳት ምክኒያት ክለቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ያልተሰለፉ ቢሆንም፣ ለዚህ ጨዋታ ግን ወደሜዳ እንደሚመለሱ ይጠበቃል። ፓል ፖግባም በቅዳሜ ዕለቱ የኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ ላይ እንዳይጫወት ካደረገው ህመም አገግሞም ወደሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

ይሁን እንጂ የዩናይትዱ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ ፊል ጆንስና ማርኮስ ሮኾ በጉዳት ምክኒያት በዚህ ጨዋታ ላይ እንደማይሰለፉ ገልፀዋል።

ለዩናይትድ ደጋፊዎች መልካሙ ዜና ወደጥሩ አቋሙ እየተመለሰ የሚገኘው አሌክሲ ሳንቼዝ በአርሰናል ቆይታው መድፈኞቹ በዚህ የውድድር ዘመን በሻምፒዮንስ ሊጉ ላይ ተሳታፊ ያልነበሩ በመሆኑ በምሽቱ ጨዋታ ላይ መሰለፍ የሚችል መሆኑ ነው።

ግምታዊ አሰላለፎች

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ሲቪያ እና ማንችስተር ዩናይትድ ይፋዊ በሆነ ውድድር ላይ ፈፅሞ ተገናኝተው ባያውቁም በ2013 ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ግን የስፔኑ ክለብ 3ለ1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ቁልፍ ፍልሚያ

ስቴቨን ንዞንዚ ከ ፓል ፖግባ

ዩናይትድ ወደኋላ አፈግፍጎ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ተግባራዊ እንደሚያደግ የሚጠበቅ በመሆኑ ይህን አጨዋወት ተግባራዊ ለማድረግ እና ቀያይ ሰይጣኖቹ ከሜዳቸው ውጪ ወሳኝ ግቦችን እንዲያስቆጥሩ የፓል ፖግባ አገልግሎት ወሳኝ ነው።

ይህ ዓይነት አጨዋወት እንዲመክን ደግሞ ፈረንሳያዊው የሃገሩ ልጅ እና የቀድሞው የስቶክ ሲቲ አማካኝ ስቴቨን ንዞንዚ ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል። ለዚህ ደግሞ ንዞንዚ በፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አብሮት የተጫዋተውን የፓግባን አጨዋወት በሚገባ ማወቁ ስለሚጠቅመው የፓግባን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማኮላሸት እንደሚጠቀምበት ይታሰባል።

ግምቶች

በምድብ ጨዋታ ላይ ሲቪያና ሊቨርፑል ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ 10 ግቦች ተቆጥረዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ጨዋታ ላይ የሞሪንሆ የጨዋታ አቀራረብ ከየርገን ክሎፕ የተለየ ነው።

የዩናይትዱ አሰልጣኝ በደርሶ መልስ ጨዋታዎች ላይ የተካኑ ናቸው። የሲቪያን ጫና በመቋቋም የመልሶ ማጥቃትን ሲጠቀሙ ደግሞ ከሲቪያም ይልቃሉ።

በውድድሩ ላይ 12 ግቦችን ማስቆጠር የቻሉት ስፔናውያኑም የዩናይትድን ጠንካራ የመከላከል ታክቲክ ሰብረውና የሚፈጠርባቸውን የመልሶ ማጥቃት በሚገባ በመሸፈን በፊት በኩል ያላቸውን ጥንካሬ በመጠቀም በዩናይትድ ላይ የሚኖራቸውን ብልጫ ሊያስመሰክሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

ግምታዊ ውጤት፡ ሲቪያ 1-1 ማንችስተር ዩናይትድ

Advertisements