በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወላይታ ድቻ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ቻለ

በካፍ ኮንፌዴሬሽን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያው ወላይታ ድቻ የዛንዚባሩን ዚማሞቶን በደርሶ መልስ ጨዋታ በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋገጠ።

የ 2018 የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጫወታዎች በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ተደርገዋል።

ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፈው የደቡቡ ወላይታ ድቻም ዚማሞቶን በአጠቃላይ ድምር ውጤት 2-1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል።

ድቻ ከሳምንት በፊት ወደ ዛንዚባር አቅንቶ በአማን ስታድየም 1-1 ተለያይቶ የተመለሰ ሲሆን ዛሬ ያደረገው የሜዳው ጨዋታ 1-0 በማሸነፉ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

ለቡድኑ በአፍሪካ መድረክ ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲሻገር ጉልህ ሚና የተጫወተው ቶጓዊው አጥቂ ጃኮ አረፋት ሲሆን ተጫዋቹ በደርሶ መልስ ቡድኑ ያስቆጠራቸውን ሁለቱን ጎሎች ከመረብ አሳርፏል።

ከጎረቤት ከተሞች ብዛት ያለው ተመልካች ወደ ሀዋሳ በማቅናት በተከታተሉት የዛሬው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ከሜዳቸው ውጪ ባስመዘገቡት ውጤት የተሻለ እድል በመያዛቸው አጋጣሚውን በሚገባ ተጠቅመውበታል።

ወላይታ ድቻ በቀጣዩ የማጣሪያ ጨዋታ የግብፁን ጠንካራ ቡድን የሆነውን ዛማሌክን የሚገጥም ይሆናል።

ዛማሌክ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ ልምድ ካላቸው እና ተደጋጋሚ ዋንጫ ካነሱ ቡድኖች መካከል አንዱ በመሆኑ ከወላይታ ድቻ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የሚጠበቅ ይሆናል።

ወላይታ ድቻም በመጀመሪያ ተሳትፎ ያስመዘገው ውጤት የሚበረታታ ሲሆን በቀጣይ የሚገጥመው ቡድን ጠንካራ በመሆኑ ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶ መዘጋጀት ይኖርበታል።

Advertisements