በርሚንግሀም / ገንዘቤ ዲባባ በ 3000ሜ የቤት ውስጥ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነች

በበርሚንግሀም የተጀመረው የአለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፕዮና ውድድር ገንዘቤ ዲባባ በ 3000ሜ በማሸነፍ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

በቤት ውስጥ ውድድር ውጤታማ በመሆን የምትታወቀው ገንዘቤ ዲባባ ምሽት ላይ በበርሚንግሀም ያደረገችውን የ 3000ሺ ሜ ውድድር አሸናፊ ሆናለች።

13 አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር ባደረጉበት ውድድር ገንዘቤ አሸናፊ የሆነችበት ሰአት 8:45:05 ሲሆን በተመሳሳይ ውድድርም ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ማሸነፍ ችላለች።

ቀድማ የወጣችውን ገንዘቤ ዲባባን ተከትለው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት የ 2016 የ 1500 አሸናፊዋ ሲፋን ሀሰን እና እንግሊዛዊቷ ላውራ ሙኒር ሲሆኑ የገቡበት ሰአትም  8:45:68 እና 8:45:78 ነው።

ገንዘቤ ዲባባ

ኬኒያዊቷ የ 5000 ሜ የአለም አሸናፊዋ ሄለን ኦቢሪ በመጨረሻ ዙር ላይ ወደ ኋላ በመቅረቷ 8:49:66 በሆነ አራተኛ ደረጃን አግኝታ አጠናቃለች።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊቷ ፋንቱ ወርቁ ደግሞ ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች።

“ለሶስተኛ ጊዜ የአለም የቤት ውስጥ ውድድር አሸናፊ በመሆኔ ተደስቻለው።ይህ ትልቅ ውድድር ነበር፣ፉክክሩም አስደናቂ ነበር፣ዛሬ ለኔና ለሀገሬ ጥሩ ቀን ነው።2017 ላይ ጥሩ አልነበርኩም ነገርግን 2018 የኔ ጊዜ ይሆናል።”በማለት ገንዘቤ ከውድድሩ በኋላ ተናግራለች።

ገንዘቤ ዲባባ ከ 2012 ጀምሮ በቤት ውስጥ ውድድር ላይ ውጤታማ ጊዜን እያሳለፈች የምትገኝ ሲሆን ይህን ጠንካራ አቋሟንን ዘንድሮም በመጀመሪያ እለት መድገም ችላለች።

ገንዘቤ 2012 ላይ በቱርክ ኢስታምቡል በ1500 ሜ የወርቅ አሸናፊ የነበረች ሲሆን 2014 እና 2016 ላይ ደግሞ በ 3000 ሜ አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏ ይታወሳል።

Advertisements