ኮንጎአዊው አጥቂ የአፍሪካ ውዱ ተጫዋች ሆነ

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተወላጁ የቀድሞ የቪያሪያል አጥቂ የአርሰናሉን ፔሪ ኤምሪክ ኦባምያንግንና የሊቨርፑሉን ሞሃመድ ሳላህን በመብለጥ የአፍሪካ ውዱ ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡

<!–more–>

ለስፔኑ ክለብ ቪያሪያል ሲጫወት የቆየው ሴድሪክ ባካምቡ ወደቻይናው ክለብ ቤጂንግ ጉዋን የተዘዋወረ ሲሆን ለዝውውሩም 65 ሚልዮን ፓውንድ ወጪ ተደርጎበታል፡፡
ተጫዋቹ ለቢጫ ሰርጓጆቹ 101 ጨዋታዎችን አድርጎ 46 ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን ባለፈው ወር ከቦሩሲያ ዶርትመንድ ወደአርሰናል በተዘዋወረው ጋቦናዊ ኦባሚያንግ የተያዘውን የ56 ሚልዮን ፓውንድ ክብረወሰን በእጁ ማስገባት ችሏል፡፡

አዲሱ የባካምቡ ክለብ ቤጂንግ ጉዋን በቀድሞው የባየርን ሊቨርኩሰን አሰልጣኝ ሮጀር ሺምዲት የሚመራ ሲሆን የባካምቡን ዝውውርም በይፋዊ ድረ ገፁ ላይ ይፋ ማድረግ ችሏል፡፡

ተጫዋቹ ለድረ ገፁ በሰጠው ቃል “ከረጅም ጥበቃ በኋላ ስለተቀላቀልኳችሁ ተደስቻለሁ ፤ ውሳኔው ቀላል አይደለም፡፡ በቪያ ሪያል ቤት ምርጥ ቆይታ ነበረኝ፡፡ አሁን ግን በዚህ ለተሻለ አገልግሎት መጥቻለሁ” ብሏል፡፡

ባካምቡና አውባሚያንግን በመከተል የሊቨርፑሎቹ መሃመድ ሳላና ሳዲዮ ማኔ ፣ እንዲሁም የማንችስተር ዩናይትዱ ኤሪክ ቤይሊ የአፍሪካ ውድ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

Advertisements