የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር በማንችስተር ሲቲ ላይ ቅጣት አስተላለፈ

ማንችስተር ሲቲ ወደ ዲ ደብሊው ስታድየም አቅንቶ ከዊጋን ጋር በኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታ አድርጎ በተሸነፈበት እለት ተጨዋቾቹ በፈጠሩት አንባጓሮ ክለቡ መቆጣጠር ባለመቻሉ በእግር ኳስ ማህበሩ ተቀጥቷል።

በሁሉም ውድድሮች ላይ ለዋንጫ እየተሳተፉ የነበሩት ማን ሲቲዎች በዊጋን ያጋጠማቸው ድንገተኛ ሽንፈት ከኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ውጪ መሆናቸው ይታወሳል።

ፋቢያን ዴልፍ በቀይ ወጥቶባቸው የተጫወቱት ሲቲዎች በባለሜዳዎቹ በተቆጠራቸው ብቸኛ ጎል ከተሸነፉ በኋላ በተጨዋቾቹ መካከል ግርግር ተፈጥሮ ነበር።

በተለይ አጉዌሮ ወደ ሜዳ ከገቡ የዊጋን ደጋፊዎች ጋር እስከመደባደብ የደረሰ ቢሆንም ከእግር ኳስ ማህበሩ ቅጣት ነፃ እንደተደረገ ይታወሳል።

ፔፕ ጓርዲዮላም እንዲሁ የዴልፍ በቀይ ካርድ መውጣት ተከትሎ ከዊጋኑ አሰልጣኝ ፖል ኩክ ጋር እሰጣገባ ውስጥ ሲገባ ተስተውሏል።

የእግርኳስ ማህበሩ ተጫዋቾችን በግል ባይቀጣም ክለቡ ግን ተጫዋቾቹን መቆጣጠር ባለመቻሉ የ50ሺ ፓውንድ ቅጣት እንዳስተላለፈ አሳውቋል።

Advertisements