“የውድድር አመቱን ለማዳን አሁንም ጊዜ አለን” – አርሴን ዌንገር

በሶስት ቀናት ውስጥ በካራባኦ ዋንጫ እና በእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ በማን ሲቲ ስድስት ጎሎች ተቆጥሮባቸው የተሸነፉት አርሴን ዌንገር ከተፎካካሪዎቻቸው በነጥብ ቢርቁም የውድድር አመቱን የማዳን ጊዜ አሁንም እንዳላቸው ተናግረዋል።

አርሰናሎች በካራባኦ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ እንዲሁም ትናንት ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ ተስተካካይ ጨዋታ በማን ሲቲ ተሸንፈዋል።

መድፈኞቹ በሁለቱ ጨዋታዎች ስድስት ጎሎችን ያስተናገዱ ሲሆን ሽንፈቱም በቡድኑ አንጋፋ አሰልጣኝ አርሴን ዌንገር ላይ ጫናው እንዲበረታ አድርጓል።

ብዛት ያለው የክለቡ ደጋፊዎችም ጨዋታውን በስታድየም ተገኝቶ ለመከታተል ባለመፈለጋቸው የኤሚሬትስ ስታድየም አብዛኛው ወንበሮች ባዶ ሆነው ታይተዋል።

የመጫወት ፍላጎት እና ትጋት ያላሳዩት መድፈኞቹ አሁንም የሚሰሯቸው ስህተቶች በቀላሉ በወቅቱ ጠንካራ የፕሪምየርሊጉ ቡድን እጃቸውን ለመስጠት ተገደዋል።

ከጨዋታው በኋላ የውድድር አመቱን ከውድቀት ለመታደግ እድል እንዳላቸው የተጠየቁት አርሴን ዌንገር “አዎ እድሉ አለን። አሁን ትኩረት ማድረግ የምንፈልገው ለቀጣዩ ጨዋታ ነው።

“በሀገሪቷ ካለ ጠንካራ ቡድን ጋር ሁለት ጊዜ ተጫውተናል ነገርግን በመጀመሪያው ጨዋታ ጥሩ ስላልነበርን ለኛ በጣም ከባድ ሆኖብናል።ነገርግን ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ስላሉን ያንን ማሳየት አለብን።” ሲሉ ተናግረዋል።

አርሰናል በቀጣይ አመት በቻምፕየንስ ሊጉ ላይ ለመሳተፍ በዩሮፓ ሊግ ላይ ዋንጫ ማግኘት ወይንም በፕሪምየርሊጉ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም በፕሪምየርሊጉ ወደ ኋላ መቅረታቸው ምናልባትም ትኩረታቸውን ወደ ዩሮፓ ሊግ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

የቡድኑ አሰልጣኝ አርሴን ዌንገርም 10 ጨዋታ በቀረው የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ በኋላ ከክለቡ ጋር የመቆየታቸው ነገር ይበልጥ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

Advertisements