“ፔፕ ጋርዲዮላ ስኬታማ እንዲሆኑ በማንችስተር ሲቲ ያለው ሁኔታ እገዛ አድርጎላቸዋል” – አንቶኒዮ ኮንቴ

ፔፕ ጋርዲዮላ ለክለባቸው ጥሩ ውጤት ለማምጣት በሚያስችላቸው ትክክለኛ መንገድ ላይ እየተጓዙ መሆኑን እና በማንችስተር ሲቲ ያለው ሁኔታም እንደረዳቸው አንቶኒዮ ኮንቴ ተናግረዋል።

የቀድሞው የባርሴሎና እና ባየር ሙኒክ አለቃ ባሳለፍነው እሁድ የካራቦኦ ዋንጫን ካገኙ በኋላ በሁለተኛ አመት የእንግሊዝ ቆይታቸው የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማሳካት በእጅጉ ተቃርበዋል።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ከጋርዲዮላ በልጠው መቀመጥ የቻሉት ኮንቴ በበኩላቸው በዘንድሮው የውድድር ዘመን ምርጥ አራት ውስጥ ሆነው ሊጉን ለማጠናቀቅ እየተውተረተሩ ይገኛል።

ከዘንድሮው የሲቲ ስኬት ጋር በተያያዘም የስኬት መነሻውን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ጣሊያናዊው የሰማያዊዎቹ አለቃ ጋርዲዮላ ከክለቡ ባለቤቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና በዝውውር መስኮቱ ላይ የነበራቸውን ተሳትፎ በምክንያትነት አቅርበዋል። 

በመጪው እሁድ በኢትሀድ ካለው ትንቅንቅ በፊት ኮንቴ በሰጡት መግለጫ “እንደማስበው ማንችስተር ሲቲ አምናም አስደናቂ ቡድን ነበር። ነገርግን ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ አሰልጣኙ የምርጥ 11 ስብስብ ለማሻሻል ጥረት አድርገው ይህ ውጤት ተገኝቷል። 

“ለዚህ ቡድን ትልቅ ክብር ሊኖረን ይገባል።  ምክንያቱም በዚህ የውድድር ዘመን እነሱ አስደናቂ ጉዞ ነበራቸው። አንዳንዴ በዚህ የሲቲ ስብስብ ውስጥ ድክመት ለማግኘት አስቸጋሪ ነው።

“እኔ እንደማስበው ጠንከረህ ስትሰራ እና በአሰልጣኙና በክለብ መሀከል ያለው መንፈስ ትልቅ ሲሆን ቡድንህን እንደፈለክ እንድታሻሽል እና በዝውውር መስኮቱ በትልቁ እንድትሳተፍ ስትደረግ ስኬታማ ትሆናለህ።” በማለት ስሜታቸውን አጋርተዋል።

Advertisements