ፖል ፑት የጊኒ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ተደርገው ተሾሙ 

ከሁለት ሳምንት በፊት ከኬንያ ብሔራዊ ቡድን ሀላፊነታቸው የለቀቁት ቤልጄማዊው ፖል ፑት የጊኒ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ተደርገው ተሾሙ።

በአፍሪካ በተለይም 2013 ላይ የቡርኪናፋሶ ብሔራዊ ቡድንን ይዘው በአፍሪካ ዋንጫ ላይ እስከ ፍፃሜ ቢጓዙም በፍፃሜ ጨዋታ ተሸንፈው ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁበት ትልቁ ስኬታቸው ነበር።

በደ/አፍሪካ ሀገራችን ኢትዮጵያ ጭምር በተሳተፈችበት የአፍሪካ ዋንጫ ዋሊያዎቹ በፖል ፑት ከሚሰለጥኑት ቡርኪናፋሶዎች ጋር በአንድ ምድብ ተደልድለው 4-0 መሸነፋቸው ይታወሳል።

የ61 አመቱ አሰልጣኝ ከጥቂት ወራት በፊት “ሀራምቤ ስታርስ”የሚባሉት የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ተደርገው ላለፉት ጥቂት ወራት ብሔራዊ ቡድኑን ሲያሰለጥኑ ቆይተዋል።

ነገርግን ከእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ባለስልጣናት ጋር መግባባት ባለመቻላቸው ከሶስት ወራት በኋላ ከሀላፊነታቸው ለቀው ላለፉት ሁለት ሳምንታት አዲስ ስራ ሲያፈላልጉ ቆይተዋል።

አሰልጣኙ ዳጎስ ባለ ደሞዝ ወደ ቻይና ሱፐርሊግ ሊያመሩ እንደሚችሉ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም ዛሬ አመሻሹ ላይ ማረፊያቸው እዚሁ አፍሪካ የጊኒ ብሔራዊ ቡድን መሆኑ ተረጋግጧል።

86 አሰልጣኞች በእጩነት በቀረቡበት ውድድር ላይ ፓል ፑት ቅድሚያውን በማግኘት ከጊኒ ጋር ለሁለት አመታት የሚያቆያቸውን ስምምነት እንደፈፀሙ ታውቋል።

ፖል ፑት

ቤልጄማዊው አሰልጣኝ በጊኒ ብሔራዊ ቡድንም ከሀላፊነታቸው የተሰናበቱት የቀድሞ አሰልጣኙ ካንፎሪ ባንጎራን ተክተው የሚሰሩ ሲሆን ለ 2019 የአፍሪካ ዋንጫ ጊኒን የማሳተፍ ሀላፊነትን ይኖርባቸዋል።

ከዛ ቀደም ብሎም መጋቢት 23 ላይ ከሞሪታኒያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርጉ ሲሆን በቀጣይ መስከረም ወር ላይ ደግሞ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር ይጫወታሉ።

አሰልጣኙ ከቡርኪናፋሶ እና ከኬኒያ በተጨማሪ ጋምቢያ እና ጆርዳንን ማሰልጠን እንደቻሉ ይታወሳል።

Advertisements