“ናፖሊ ከባርሴሎና የተሻለ ነው” – ጂያኒኒ

የቀድሞው የሮማ ታሪካዊ ተጫዋች የሆነው ጁሴፔ ጂያኒኒ የዛሬ ምሽት ተፋላሚያቸው ናፖሊ “ከባርሴሎና የተሻለ የሚጫወት” ክለብ መሆኑን ገልፀዋል።

ፓርቶኖፔዎቹ አራት ጨዋታዎችን ብቻ በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ በተከታታይ 10 ጨዋታዎችን በማሸነፍ በአሁኑ ጊዜ በሴሪ አው የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ይገኛሉ።

“ናፖሊ ከባርሴሎና የተሻለ ይጫወታል። ሲሉ ጂያኒኒ ለጣሊያኑ ኮሪየር ዴል ሜዞጊዮርኖ ጋዜጣ ተናግረዋል።

“የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴያቸውና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ያለው አጨዋወታቸው ከስፔናውያኑ በተሻለ ውጤታማ ነው። የዲያጎ ማራዶናው ቡድን ስኩዴቶውን ሲያሸንፍ አስደናቂ የፊት አጥቂ ያለውና የቡድን ስራ ጥንካሬ ያለው የዓለማችን ምርጥ ቡድን ነበር።

“እንቅስቃሴያቸው የሚጀምረውም ከተከላካይ ክፍል ሲሆን በኮንሰርት ላይ የሙዚቃ መሳሪያ ቅንጅት እንዳለው ኦርኬስትራም ነው።

“ናፖሊ ስኩዴቶውን ማሸነፍ የሚችልበት ዕድል አለው። ጁቬንትስም የማሸነፍ ልምድ እና ድንቅ ብቃት አለው። ያለምንም ጥርጥርም የበላይ የሆነ የቡድን ስብስብ አላቸው። ነገር ግን አዙሪዎቹ ማንኛውንም ነገር የማድረግ አቅም አላቸው።

“የዛኑ ያህል ለሮማም ትክክለኛው ጨዋታ ነው። ለሻምፒዮስ ሊጉ ማለፍ ካለባቸው ጠንካራ ተፎካካሪያዎቻቸውን ላዚዮን፣ ኢንተርና ሚለንን ተመልክተው በቀጥታ ወደቀድሞ ብቃታቸው መመለስ ይጠበቅባቸዋል።” ሲሉ ተናግረዋል።

በሴሪ አው ሮማ ዛሬ (ቅዳሜ) ምሽት ናፖሊን ከሜዳው ውጪ የሚገጥም ይሆናል። በሌላ የዛሬ ምሽት ትልቅ የሴሪ ኣ ጨዋታም ላዚዮ ጁቬንቱስን ይገጥማል።

Advertisements