አስደንጋጭ / አትሌት ጫላ አዱኛ በድንገተኛ አደጋ ህይወቱ አለፈ

አትሌት ጫላ አዱኛ በልምምድ ላይ ባጋጠመው ድንገተኛ አደጋ ህይወቱ አልፏል።

የማራቶን ሯጭ የነበረው ጫላ በትናንትናው እለት ልምምድ በማድረግ ላይ እያለ በድንገት ተበጥሶ የተንጠለጠለ የኤሌክትሪክ ገመድ በመያዙ ምክንያት ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል።

አትሌት ጫላ አዱኛ የኦሮሚያ ማረሚያ ክለብን በቅርቡ የተቀላቀለ ተስፈኛ ሯጭ የነበረ ሲሆን በተለያዩ የግል ውድድሮች ላይ በመካፈልም አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

በቅርቡም ሞሮኮ ማራካሽ በተካሄደ የማራቶን ውድድር ላይ 2 ሰዓት ከ 11 ደቂቃ ከ47 ሰከንድ መግባት የቻለ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጉዳዩን በማስመልከት በላከው የሀዘን መግለጫ ደብዳቤ ላይ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለመገናኛ ብዙሀን አካላት በላከው የሀዘን መግለጫ በክስተቱ የተሰማውን ሀዘን ገልፆ ለአትሌቱ ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን ተመኝቷል።

አትሌት ጫላ በጀርመን ሃኖቨር በተካሄደው የማራቶን ውድድር ላይም 2 ሰዓት ከ 09 ደቂቃ ከ 42 ሰከንድ ውድድሩን በመጨረስ የግሉን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ የቻለ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያን በማራቶን ውድድርን ለመወከል ተስፋ ተጥሎበት የነበረው አትሌቱ በደረሰበት ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን የገለፀው አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ለቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ተመኝቷል።

Advertisements