ከቻምፕየንስ ሊጉ ጨዋታ በፊት የኬሲሲኤ ዎቹ አማካዮች ሙትያባ እና ፖሎቶ ከጉዳት ተመለሱ  

የፊታችን ረቡእ በአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ ቅ/ጊዮርጊስን የሚገጥመው የዩጋንዳው ኬሲሲኤ አማካዮች ሙዛሚር ሙትያባ እና ጁሊየስ ፖሎቶ ከጉዳት መመለሳቸው መልካም ዜና ሆኖላቸዋል።

ፈረሰኞቹን ለመግጠም ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት የዩጋንዳ ፕሪምየርሊግ 18ኛ ጨዋታውን ያደረገው ኬሲሲኤ በማሸነፉ ወደ ሊጉ መሪነት ተጠግቷል።

3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ሶዋናን የገጠመው የአምናው ሻምፒዮን ኬ ሲ ሲ ኤ ወደ አሸናፊነትን የተመለሰበት ብቸኛ ጎልን ያገኘው በመስመር አማካዩ ፖሎቶ ነው።

አማካዩ በቻምፕየንስ ሊጉ የማዳጋስካሩን ስናፕ ስፖርትን ሲገጥሙ ጉዳት ካስተናገደ በኋላ ወደ ሜዳ ያልተመለሰ ሲሆን ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ሜዳ በተመለሰበት የዛሬው ጨዋታ ላይ የቡድኑን ብቸኛ ጎል በማስቆጠር ወደ ሊጉ አናት ላይ እንዲጠጉ አድርጓል።

ሌላው ከጉዳት የተመለሰው የአጥቂ አማካዩ ሙዛሚር ሙትያባ ሲሆን ተጫዋቹ በጉዳት ከታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ ቡድኑን ማገልገል ሳይችል ቀርቶ ነበር።

“በመጀመሪያ ፈጣሪን፣አሰልጣኛችን፣ የቡድኑን ሀኪምን እና የቡድን ጓደኞቼን በድጋሚ ኳስ ለመምታት እንድችል ስላደረጉኝ ላመሰግን እፈልጋለው።

“በእግርኳስ ሁልጊዜ ሜዳ ውስጥ መገኘት አለብህ፣ከሜዳ ውጪ ያሳከፍኳቸው ያለፉት ጊዜያት በጣም ከባድ ነበሩ ነገርግን ያሁሉ አሁን አልፎ ተመልሻለው።” ሲል ሙትያባ ተናግሯል።

በአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ ቅ/ጊዮርጊስ እና ኬሲሲኤ የፊታችን እሮብ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በ አ/አ ካደረጉ በኋላ የመልሱን ጨዋታ በዩጋንዳ ያደርጋሉ።

ኬሲሲኤ የተጎዱ ተጫዋቾቻቸው በማግኘታቸው እና ወደ ሊጉ መሪነት በመመለሳቸው  ከቅ/ጊዮርጊስ የዘንድሮ አቋም መውረድ ጋር ተደምሮ ለፈረሰኞቹ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።