ፊፋ በቪድዮ የታገዘ ዳኝነት በራሺያው የአለም ዋንጫ ላይ እንዲሰራ አፀደቀ

ፊፋየፊታችን ሰኔ ወር ላይ የሚጀመረው የ 2018 የራሺያው የአለም ዋንጫ ላይ በቪድዮ የታገዘ ዳኝነት(VAR) ስራ ላይ እንዲውል የቀረበውን ረቂቅ አፅድቋል።

ከአራት ወራት ያነሰ ጊዜያት የቀረው 32 ሀገራት የሚሳተፉበት የ2018 የአለም ዋንጫ በራሺያ ይካሄዳል።

ፊፋ ባለፉት ወራት በተለያዩ ሀገራት እየተሞከረ የሚገኘውን በቪድዮ የታገዘ ዳኝነት ከገመገመ በኋላ በአለም ዋንጫው ላይ እንዲተገበር እንደወሰነ ታውቋል።

ዛሬ በስዊዘርላንድ ዙሪክ የተካሄደው 132 ኛው አለም አቀፍ የእግርኳስ ማህበራት ቦርድ አመታዊ ስብሰባ ላይ በጉዳዩ ላይ ውይይት ከተደረገበት በኋላ የቪድዮ ቴክኖሎጂው በአለም ዋንጫ ላይ እንዲያገለግል ተወስኗል።

አለም አቀፍ የእግርኳስ ማህበራት ቦርድ እንዳሳወቀው ከሆነ “በዳኝነት የታገዘ የቪድዮ ቴክኖሎጂ ፍልስፍና በጥቂት ጣልቃ ገብነት ብዙ ጥቅም የሚገኝበት” ነው በማለት አላማው ግልፅ የሆኑ ፍትሀዊ ያልሆኑ ስህተቶችን ለመቀነስ እንዲሁም ያልታዩ አንገብጋቢ ክስተቶችን ለመመልከት እንደሆነ አሳውቋል።

ፊፋ መጋቢት 16 በሚያደርገው ስብሰባ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔውን እንደሚየሳውቅ የሚጠበቅ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ አዲስ ሀሳብ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም።

አዲሱ አሰራር በሩሲያው አለም ዋንጫ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በአለም ላይ ባሉ ሊጎች ላይ ተግባራዊ መሆኑ እንደሚቀጥል የተነገረ ቢሆንም የዳኞችን አሰራር በመጫን እና

የጨዋታውን ፍሰት በማስተጓጎል እንዲሁም በተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ላይ ብዥታን በመፍጠር ችግር እንዳይፈጥር ተሰግቷል።

የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ክለቦችም በቀጣዩ ወር በሚያደርጉት ውይይት ላይ በፕሪምየርሊጉ ለወደፊት በቪድዮ የታገዘ ዳኝነት ስለመኖሩ ውሳኔ ያስተላልፋሉ።

Advertisements