በአለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አንፀባራቂ ድል አስመዘገቡ


በበርሚንግሃም እየተካሄደ ባለው የአለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የዛሬ ውሎ ኢትዮጵያ በዮሚፍ ቀጀልቻ(3000 ሜትር) እና በሳሙኤል ተፈራ(1500 ሜትር) ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ማግኘት ችላለች፡፡

በወንዶች 3000 ሜትር ከሁለት አመት በፊት የተካሄደውን ውድድር በአንደኝነትና በሁለተኝነት ያጠናቀቁት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ሰለሞን ባረጋ በድጋሚ ያንን ገድል በመድገም የወርቅና የብር ሜዳልያውን ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል፡፡

ዮሚፍ ውድድሩን በአንደኝነት ለማጠናቀቅ 8:14:41 ደቂቃ የፈጀበት ሲሆን እሱን ተከትሎ የገባው ሰለሞን ባረጋ 8:15:59 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡

ኬንያዊው ቤዝዌል ቢርገን ኢትዮጵያውያኑን ተከትሎ በሶስተኝነት ውድድሩን አጠናቋል፡፡


ከዚህ ቀደም ብሎ የተካሄደው የወንዶች 1500 ሜትር ውድድር ለኢትዮጵያ ሌላኛውን ወርቅ ያስገኘ ሲሆን ሳሙኤል ተፈራ ውድድሩን በ3:58:18 በመጨረስ አራተኛውን ወርቅ ለአገሩ አስገኝቷል፡፡ ከሳሙኤል በመከተል ፖላንዳዊው ማርሲን ሌዋንዶውስኪ በሁለተኝነት ርቀቱን የፈፀመ ሲሆን ሞሮኮ በአብደላቲ ኢጉይደር አማካኝነት ነሃስ አግኝታለች፡፡
ኢትዮጵያ በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ ያገኘቻቸውን ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ጨምሮ አራት ወርቆችን በማስመዝገብ በበርሚንግሃሙ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና መልካም ጊዜን እያሳለፈች ትገኛለች፡፡

Advertisements