ባርሴሎና ከ አትሌቲኮ ማድሪድ | የጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ

በላ ሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ተከታትለው የተቀመጡት ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ በኑ ካምፕ እሁድ አመሻሹ ላይ የሚያዳረጉት ጨዋታ በውድድር ዘመኑን የላ ሊጋ ክብርን ለመቀዳጀት የሚደረገውን ፉክክር ይበልጥ ለማስፋት ወይም ይበልጥ ለማጥበብ የሚያደረጉት ይሆናል።

የኤርነስቶ ቫልቬርዴው ቡድን በሳምንቱ አጋማሽ ከላስ ፓልማስ ጋር ያደረገውን ጨዋት 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በአንፃሩ አትሌቲኮ ማድሪድ ረቡዕ ምሽት ሌጋኔስን 4ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በመካከላቸው ያነበረውን ሰባት የነጥብ ልዩነት ወደአምስት ማጥበብ ችሏል።

የቀደሙ ግንኙነቶቻቸው

አትሌቲኮ ማድሪድ ለመጨረሻ ጊዜ ወደኑ ካምፕ ተጉዞ መጫወት የቻለው በፈረንጆቹ ያለፈው ዓመት የካቲት 2017 ቢሆንም ጨዋታውን ግን በመልካም ውጤት ማጥናቀቅ አልተቻለውም።

አትሌቲኮ በዚህ የኮፓ ዴል ሬይ የግማሽ ፍፃሜ የደርሶ መልስ የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳው ላይ 2ለ1 ከተሸነፈ በኋላ የመልሱ ጨዋታ በበርካታ ቀይካርዶች እና የፍፁም ቅጣት ምት የማምከን ድራማዊ ክስተቶች ታይተውበት ባርሴሎና ለፍፃሜው መብቃት እንዲችል ሆኗል።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረ የልዊስ ስዋሬዝ ግብ ባለሜዳው ለፍፃሜ ቢበቃም፣ ሰርጂ ሮቤርቶ እና የኒክ ካራስኮ ከሁለቱም ክለቦች በኩል ቀይ ካርድ ተመልክተዋል።

የጨዋታው ምሽት ለአትሌቲኮዎች መልካም ያልነበረ ሲሆን፣ አንቱዋን ግሪዝማን በስህተት ከጨዋታው ውጪ ነው ሲባል፣ ጋሜሮ ደግሞ የፍፁም ቅጣት ምት አምክኗል።

እንዲሁም ልዊስ ስዋሬዝ በቀይ ካርድ ሊያሰናብተው የሚችለው ጥፋት ፈፅሞ የነበረ ቢሆንም በዳኛው ውሳኔ ከስንብት ተርፏል።

ቁልፍ ፍልሚያ

ሳሙኤል ኡምቲቲ ከ አንቱዋን ግሪዝማን

ምንም እንኳ ሁለቱ ተጫዋቾች በፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ላይ አጋር ሆነው የሚጫወቱ ቢሆንም፣ ኡምቲቲ በእሁድ ምሽቱ ጨዋታ አንቱን ግሪያዝማንን ለማስቆም ሲል አጋርነታቸውን ወደጎን ለማለት ይገደዳል።

የቀድሞው የሪያል ሶሴዳድ ተጫዋቹ ግሪዝማን ባለፉት ሁለት የላ ሊጋ ጨዋታዎቹ ሰባት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ በአሁኑ ጊዜ አስደንቂ የብቃት ደረጃ ላይ ይገኛል። ያለምንም ጥርጥርም የሲሞኒው ቡድን ቁልፍ ተጫዋች እሱ ነው። በመሆኑም የቀድሞው የሊዮን ተጫዋች ኡምቲቲ በእሁዱ ጨዋታ የግሪዝማንን ወቅታዊ አስደናቂ ብቃት የመግታት ኃለፊነት ተጥሎበታል።

የቡድን ዜናዎች

ቬልቬርዴ ከሀሙሱ የላስ ፓልማስ ጨዋታ ወዲህ በቡድናቸው ላይ ምንም አይነት አዲስ የጉዳት ችግር የለባቸውም። ይሁን እንጂ ከዚያ ቀደም በጉዳት ላይ የነበሩት ኔልሰን ሳሜዶ (በቋንጃ)ና ሰርጂ ሳምፔር (በቁርጭምጭሚት) በእሁዱ ጨዋታ ላይ አይሰለፉም።

በሌላ በኩል በሲሞንው ቡድን በኩል ያለው ብቸኛ ጉዳት የቋንጃ ጉዳት ያለበት አርጄንቲናዊው ሉካስ ሄርናንዴዝ ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ

የባርሴሎና ግምታዊ የመጀመሪያ አሰላለፍ፡ ቴር ሽቴጋን፣ ሮቤርቶ፣ ፒኬ፣ ኡምቲቲ፣ አልባ፣ ቡስኬት፣ ኢንየስታ፣ ፓውሊንሆ፣ መሲ፣ ሱዋሬዝ፣ ኮቲንሆ

የአትሌቲኮ ማድሪድ ግምታዊ የመጀመሪያ አሰላለፍ፡ ኦብላክ፣ ኹዋንፍራን፣ ጊሜኔዝ፣ ጎዲን፣ ፊሊፔ ልዊስ፣ ኮኬ፣ ቶማስ፣ ሳኡል፣ ኮሬራ፣ ግሪዝማን

ግምቶች

ሁለቱም ቡድኖች ለላ ሊጋው ዋንጫ በቅርብ ርቀት የሚፎካከሩ ክለቦች እንደመሆናቸው የእሁዱን ጨዋታ ማሸነፍ ያለውን ፋይዳ ጠንቅቀው ያውቁታል።

ጨዋታውን ማሸነፍ ባርሴሎንን ፉክክሩን በስምንት ነጥቦች በመራቅ እንዲመራ ሲያስችለው፣ አትሌቲኮን ደግሞ ፉክክሩን በሁለት ነጥቦች ብቻ ከማጥበቡም በላይ እግረመንገዱንም የዚህ የውድድር ዘመን የባርሴሎናን ያለመሸነፍ ጉዞ ክብረወሰን እንዲያበቃ ማደርግ ያስችለዋል።

ምንም እንኳ ጨዋታው ወሳኝ ቢሆንም ሁለቱም ክለቦች በጨዋታው ላይ ሽንፈት እንዲደርስባቸው ጨርሶ አይፈልጉም። በመሆኑም ጨዋታው በእጅጉ በታክቲክ ላይ የተመሰረተ እና ጥንቃቄ የበዛበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የጨዋታው ግምታዊ ውጤት፡ ባርሴሎና 1-1 አትሌቲኮ ማድሪድ

Advertisements