ፎንቴ፣ጋይታን እና ካራስኮ በቻይና ሱፐርሊግ የመጀመሪያ ጨዋታቸው አሳፋሪ ሽንፈት አጋጠማቸው

በከፍተኛ ሳምንታዊ ደሞዝ ወደ ቻይና አቅንተው ለዳሊያን ይፋን ፊርማቸውን ያኖሩት በአውሮፓ ለታላላቅ ቡድኖች የተጫወቱት ጆሴ ፎንቴ፣ኒኮላስ ጋይታን እና ያኒክ ካራስኮ በመጀመሪያ ጨዋታቸው      8 -0 ተሸነፉ።

የአውሮፓ ተጫዋቾች ወደ ቻይና ሲያቀኑ የመጀመሪያቸው ባይሆንም ወደ እዛ የመሄዳቸው ሚስጢር ግን ዳጎስ ያለ ደሞዝ ለማግኘት እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማሙበታል።

በተለይም የላቲን አሜሪካ እና የአፍሪካ ተጫዋቾች በሀገራቸው ያሳለፉትን የድህነት ቀንበር ለመስበር ከቻይና የሚቀርብላቸውን ደሞዝ እና ጥቅማቅሞች ለመቀበል ሲገደዱ ይታያሉ።

ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ በአውሮፓ ኑሯቸውን ያደላደሉ ተጫዋቾች ጨምሮ ወደ ቻይና የሚያቀኑ የተጫዋቾች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

ካርሎስ ቴቬዝ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ በድጋሚ ወደ ቻይና በማቅናት ሳምንታዊ 650ሺ ፓውንድ ሲከፈለው እንደነበር ይታወሳል።

በቅርቡም በተመሳሳይ በሳውዝሀምተን እና በዌስትሀም የተጫወተው ጆሴ ፎንቴ እንዲሁም የአትሌቲኮ ማድሪዶቹ ኒኮላስ ጋይታን እና ያኒክ ካራስኮ ወደ ቻይና አቅንተው ዳሊያን ይፋን ለሚባል ክለብ መፈረማቸው ይታወሳል።

ሶስቱ ተጫዋቾች ትናንት ኦስካርን እና ሀልክን ከያዘው ሻንጋይ ኤስ አይ ፒ ጂ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ቢያደርጉም 8-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ተሸንፈዋል።

ይህ ሽንፈታቸው ደግሞ ከፍተኛ ደሞዝ ለመክፈል ተጫዋቾቹን ያዘዋወረው ዳሊያን ይፋን ክለብ ትችት እንዲያስተናግድ አድርጎታል።

በተለይ ሳምንታዊ 170 ሺ ፓውንድ የሚከፈለው ያኒክ ካራስኮ በጨዋታው ላይ የነበረው ተሳትፎ እና የነካው የኳስ ብዛት ውስን መሆኑ ጠንካራ ትችት አስተናግዷል።

የቀድሞ የቼልሲ ተጫዋች የነበረው ኦስካር ለሻንጋይ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ሀትሪክ መስራት ችሏል።

Advertisements