ሆዜ ሞሪንሆ ክረምቱ የዓለም ዋንጫ ለሩሲያው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተንታኝ ሆነው ሊሰሩ ነው

ሆዜ ሞሪንሆ በመጪው ክረምት በሚዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ለሩሲያው የመገናኛ ብዙኃን ማሰራጫ ለሆነው አርቲ ቲቪ የጨዋታ ራትንታኔ ባለሙያ ሆነው የሚሰሩ ይሆናል።

የማንችስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ” በሃገሪቱ መንግስት የገንዘብ ምንጭ ለሚተዳደረው የቴሌቭዥን ጣቢያ “ሙያዊ ትንተና እና የውጤት ግምታቸውን” እንደሚያቀርቡ አርቲ ገልፅዋል።

“የአርቲን ቡድን በመቀላቀሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። በመጪው ክረምት በሩሲያው ዓለም ዋንጫ ላይ ለመታደም እና በጨዋታዎቹ ላይ ያለኝን ምልከታ ለማቅረብ እቅድ አለኝ።” ሲሉም ሞሪንሆ በአርቲ ድረገፅ በኩል ገልፀዋል።

የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ፒተር ሽሜይክልም በሩሲያ በሚዘጋጀው ውድድር ላይ ለአርቲ ቲቪ በተንታኝነት የሚሰራ ሌላኛው ሰው ነው።

“የአርቲን ሃሳባዊ ምርጥ ቡድን በጋራ መስራታችንን እንቀጥላለን። እናም አሁን አሰልጣኛችንን አግኝተናል።” ሲሉ የሩሲያ ቱደይ ጋዜጣ ዋና ኤዲተር የሆኑት ማርጋሪታ ሲሞንያን ተናግረዋል።

አርቲ የእንግሊዘኛ ቋንቋ የዜና አገልግሎት መሰረቱን በዌስትሚንስቴር ያደረገ እና ከዚህ ቀደም በቭላድሚትር ፑቲን እና በሩሲያ መንግስት ቃልአቀባይ እንደሆነ ወቀሳ ሲደርስበት የቆየ የቴሌፅቭዥን ጣቢያ ነው።

Advertisements