“ቼልሲ ያሳየው እንቅስቃሴ እግርኳስን ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው” – ጄሚ ሬድናፕ

የአንቶኒዮ ኮንቴው ቼልሲ ወደ ኢትሀድ አቅንቶ በማን ሲቲ ሙሉ ብልጫ ተወስዶበት የተሸነፈበት ጨዋታ ያሳየው እንቅስቃሴ በእግርኳስ ተንታኞች ጠንካራ ትችት እየቀረበበት ይገኛል።

ዋንጫውን በይፋ ማንሳት ብቻ የቀረው የፔፕ ጓርዲዮላው ቡድን የፕሪምየርሊጉን ትላልቅ ቡድኖችን እንደ ትንሽ ቡድኖች በሜዳቸውም ይሁን ከሜዳቸው ውጪ እያሸነፈ ይገኛል።

አርሰናሎችን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ አንገታቸውን ዝቅ እንዲያደርጉ ካደረጉ በኋላ ትናንት ደግሞ ተረኛው ቼልሲ ሆኗል።

ሰማያዊዎቹ ምንም እንኳን የአርሰናል ያህልን ጎል አስተናግደው ባይሸነፉም በጨዋታው የነበራቸው እንቅስቃሴ ጨዋታውን ለማሸነፍ ፍላጎት እንዳልነበራቸው መረዳት ይቻላል።

ባለሜዳዎቹ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር የአንቶኒዮ ኮንቴውን ቡድን በማሸነፍ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እጅግ ተቃርበዋል።

የሚገርመው ቼልሲ ከሲቲ የተሻለ እረፍት አድርጎ መጥቶ ይህን ያህል በእንቅስቃሴ መበለጡ የቀድሞ ተጫዋቾች፣የእግርኳስ ተንታኞች ትችታቸውን ቡድኑ ላይ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል።

ከነዚህም ውስጥ ጄሚ ሬድናፕ እና ጋሪ ኔቭል የሚጠቀሱ ሲሆን በተለይ ሬድናፕ “የቼልሲ ያሳየው እንቅስቃሴ ከእግርኳስ በተቃራኒ የቆመ ወንጀል ነው” ሲል ገልፆታል።

“እንቅስቃሴያቸው ፀረ እግርኳስ ነበር።በእግርኳስ ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነበር።ጨዋታውን ለመመልከት ጓጉቼ ነበር፣ ነገርግን በተመለከትኩት ነገር በጣም ተሰምቶኛል።ያለ አጥቂ መጫወት ለማሸነፍ ከባድ እንደሚያደርገው እረዳለው፣ነገርግን ትንሽ ፍላጎት ልታሳይ ይገባል።ቡድኑ ጥሩ ተጫዋቾች አሉት ነገርግን ወደፊት ለመጓዝ ፍላጎት አልነበራቸውም።” ሲል ጠንካራ ትችት አቅርቧል።

አንቶኒዮ ኮንቴ በጨዋታው ላይ ሀዛርድን በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ከማሰለፍ ውጪ መደበኛ የአጥቂ ተሰላፊዎቻቸውን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አድርገው አልጀመሩም።

Advertisements