“እውነታውን መቀበል አሊያም ደግሞ በአርሰናል ቤት የረጅም ጊዜ ቀውስ ለማስተናገድ መዘጋጀት አለብን” – ጆሽ ክሮንኬ

የአርሰናል ክለብ ትልቅ ባለድርሻ የሆኑት ስታን ክሮንኬ ልጅ ጆሽ ክሮንኬ ክለቡ እውነታውን መቀበል አሊያም ደግሞ የረጅም ጊዜ ቀውስን ለማስተናገድ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረዋል። 

የአሜሪካዊው ከበርቴ ልጅ የተጠናቀቀውን የፈረንጆች ወር የፕሪምየር ሊግ ክለብ እንዴት ይተዳደራል በሚለው ላይ ጥናት ለማድረግ በለንደን ከትመው ቆይተዋል።

በለንደን ቆይታቸውም መድፈኞቹ በካራባኦ ዋንጫ ፍፃሜ በማንችስተር ሲቲ ተሸንፈው ዋንጫውን ሲነጠቁና ባሳለፍነው እሁድ በተከታታይ ለአራተኛ ጨዋታ ለብራይተን እጅ ሲሰጡ ጆሽ ለመመልከት ተገደዋል። 

የኢምሬትሱ ክለብ ከከባድ የውጤት ማሽቆልቆሉ ጋር በተያያዘም ምርጥ አራት ውስጥ ሆኖ በመጨረስ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን የማግኘቱ ነገር ዳግም ለሁለተኛ ተከታታይ አመት የማይሳካ አይነት መስሏል። 

ከነዚህ ሁነቶች ጋር በተያያዘም የአሰልጣኝ አርሰን ቬንገር የኢምሬትስ ቆይታ እያበቃለት መሆኑ በስፋት እየተነገረ ሲሆን አንዳንድ ዘገባዎችም ክለቡ በመጪው ክረምት አሰልጣኝ ለመቀየር እያሰበ መሆኑን እያተቱ ይገኛል። 

ጆሽ ‘ዎጅ ፖድ’ ከተሰኘ አንድ የአጭር ሰዓት ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታም በአርሰናል ቤት በሰላም ድል ማምጣት የሚል መፈክር እንዳለ ነገርግን እሱን ለማሳካት መግባባት እና ነገሮችን በግልፅነት መቀበል ቀዳሚ ነገር መሆኑን ተናግረዋል።

ሰውየው በንግግራቸው “በእውነታው ላይ ግልፅ እና ትክክለኛ ውይይት ሊደረግ ይገባል። ምክንያቱም ስለራሳችን፣ ስለቡድናችን፣ ስለአቅጣጫችን ሁሉም ነገር ጥሩ ነው ብለን ካልን እራሳችንን እያጃጃልን እና የረጅም ጊዜ ችግር እየፈጠርን ነው።” ሲሉ ከአሁኑ እውነታውን መቀበልና መፍትሄ መፈለግ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።

ጆሽ እስካሁን ድረስ በአርሰናል ዙሪያ ያላቸው ጣልቃ ገብነት በጣም አነስተኛ ሆኖ ቢቆይም ቤተሰቦቻቸው ባለቤት በሆኑባቸው እንደ ቅርጫት ኳስ አይነት ሌሎች ክለቦች ትልቅ ተሳትፎ አላቸው። 

Advertisements