“ኦክስሌድ ቻምበርሌን በሊቨርፑል እያደረገው ለሚገኘው ነገር አድናቆት ሊቸረው ይገባል።” ቴሪ ሆነሪ

የቀድሞው የአርሰናል ዝነኛ ተጫዋች ቴሪ ሆነሪ የሊቨርፑሉ ተጫዋች አሌክስ ኦክስኬድ-ቻምበርሊን ለአርሰናል ያደረገውን የተለየ ነገር ማየት ስላለመቻሉ የሰጠውን አስትያየት ባይቀይርም፣ ነገር ግን በሊቨርፑል እያሳየ የሚገኘውን ነገር በግልፅ እያየ በመሆኑ ለተጫዋቹ አድናቆት ሊቸረው እንደሚገባ ተናግሯል።

የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ በስካይ ስፖርት የቴሌቭዥን ጣቢያ “ኦክስሌድ ቻምበርሌን በእስካሁኑ የሊቨርፑል አጭር ጊዜ ቆይታው ላደረገው ነገር አድናቆት ሊቸረው ይገባል። ነገር ግን ይህን በአርሰናል በግልፅ አልተመለከትንም።

“በእኔ አገለለፅ የፍራንክ ላምፓርድን ምሳሌ ብጠቀም ሁሉም ሰው የሱን ጥሩ ነገር ያውቀል። የላምፓርድ ብቃት ከኋላ በጥልቀት ተነስቶ የሚጫወት መሆኑ ላይ ነው፤ በእንቅስቃሴ ላይም ወደኋላ ቀርቶ ግቦችን ያስቆጥራል፤ እንዲሁም በርካታ የግብ ዕድሎችንም ይፈጥራል።

“በአርሰናል የአክስሌድ-ቻምበርሌን የተሻለ የመጫወቻ ቦታ የት ነው የሚለው ሁልጊዜም አከራካሪ ጉዳይ ነበር። አንድ ቀን የኋላ ክንፍ ተጫዋች ይሆናል። አንድ ቀን ደግሞ የግራ ክንፍ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የቀኝ ክንፍ እንዲሁ በሌላ ቀን ደግሞ 10 ቁጥር ይሆናል። እኛ ያለወቅንው ችግርም ያ ነበር።

“አንተ በተረጋጋ ቦታ ላይ በተደጋጋሚ ካልተጫወትክ ደግሞ ማንነትህን እና በምን ላይ ጥሩ እንደሆንክ መረደት በጣም አስቸጋሪ ነው። የብቃትህን ደረጃ ወደፊት ማስቀጠል እና ከፍ ያለ ደረጃ ላይ መድረስም በጣም ይከብድሃል። እሱ በፕሪሚየር ሊጉ ለአርሰናል በተጫወተባቸው 132 ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው ዘጠኝ ግብ ሲሆን ለግብ ያመቻችቸው ደግሞ 14 ብቻ ነበር። ነገር ግን ለሊቨርፑል ከወዲሁ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት የግብ ዕድሎችንም አመቻችቷል።

“አሁን በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ግልፅ ነገሮችን እና እንዲያደርግ የሚጠበቅበትን ነገር ማየት እንችላለን። ለዚህ ሁሉ ተመስጋኙ ሰው ደግሞ የርገን ክሎፕ እና ራሱ ኦክስሌድ-ቻምበርሌን ነው።” ብሏል።

ፈረንሳያዊው የቀድሞ የመድፈኞቹ አጥቂ ስለእንግሊዛዊው ተጫዋች የአጨዋወት መንገድ ሲገልፅም “በሊቨርፑል በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም አጋጣሚ በተቃራኒ ቡድን ላይ ጫና የሚፈጥር አማካኝ እየተመለከትን ነው። ኳስንም መልሶ ይነጥቃል፤ ግቦችን ያስቆጥራል የግብ ዕድሎችንም ያመቻቻል። አሁን እሱ ምን ዓይነት ተጫዋች እንደሆነ በግልፅ መመልከት እንችላልን።” ብሏል።

በስካይ ስፓርት የቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ የጨዋታ ተንታኝ በመሆን እየሰራ የሚገኘው ሄነሪ ኦክስሌድ-ቻምበርሌን አሁን ያለውን ጥሩ ብቃት አውጥቶ ማሳየት እንዲችል ያደረጉት ጀርመናዊው የቀዮቹ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ መሆናቸውንም ጭምር ተናግሯል።

“ለክሎፕም ምስጋነውን ልትቸር ይገባል። ምክኒያቱም [ስለመለወጡ መናገር የሚቻለው] ኦክስሌድ-ቻምበርሌን ብቻ አይደለም። ስለአንድሪው ሮበርትሰን፣ ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ እና የሊቨርፑልን አጨዋወት ስለተላመዱት ሌሎች ተጫዋቾችም ልትናገር ትችላለህ።”

ሄነሪ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቹ ኦክስሌድ-ቻምበርሌን ጥሩ ብቃቱን የሚቀጥል ከሆነ ከቀድሞው የተሻለ ተጫዋች እንደሆነም ይናገራል።

“በሊቨርፑል ምን አይነት ተጫዋች ሊሆን እንደሚችል አሁን መመልክት ችለናል። [ከዚህ ቀደም] ሁልጊዜም ብቃቱ ነበረው። አሁን ደግሞ በሚደንቅ ሁኔታ ጥሩ እየተጫወተ ይገኛል። አሁን ያለውን የማግባት እና ግብ የማመቻቸት የቁጥር መጠን ከቀጠለበት በአርሰናል ማሳካት የቻለውን የቁጥር መጠን በቀላሉ ማለፍ ይችላል።” ሲል ሄነሪ ገልፅዋል።

ኦክስሌድ-ቻምበርሌን ሊቨርፑል ዛሬ (ማክሰኞ) ምሽት 16 ክለቦች ተሳታፊ በሆኑበት የሻምፒዮንስ ሊጉ የጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታ ፓርቶን በአንፊልድ ሲገጥም አሁንም በአማካኝ ስፍራ ላይ ተሰልፎ እንደሚጫወት ይጠበቃል።

Advertisements